“ከደደቢት ጋር በነበረኝ ጨዋታ አፍንጫዬና ጥርሴን በድንጋይ ተመትቼ ጥርሴን ለማስተካከል 2 ጊዜ ተነቅሼያለሁ” አይናለም ኃይለ (ፋሲል ከነማ)

“ቀሪ 6 ጨዋታዎችን ትኩረት ሰጥቶ በመጫወት ዋንጫውን እንደምናነሳ እርግጠኛ ነኝ”

በጎንደር ከተማ ሰፖርት አፍቃሪ በተለይ በፋሲል ከነማ ደጋፊዎች በጣም ይወደዳል… ፍቅራቸው የገለፁለትን ደጋፊዎች ለመካስ እንዳይችል ግን ባለፉት 300 ቀናት የገጠመው ጉዳት እክል ሆኖበት ቆይቷል፡፡ ከሰሞኑ ግን ከህመሙ ጋር ታግሎ በማሸነፍ ከ10 ወራት ጉዳት በኋላ ወደ ጨዋታ የተመለሰው አይናለም ኃይለ ባለፉት አራት ጨዋታዎች እየተቀየረ በመግባት የፋሲል ከነማ ድል ላይ ራሱን የቻለ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ቆይታ የነበረው አይናለም ስለጉዳቱ ጊዜ አሁን ስላለበት ደረጃና ቀጣይ የክለቡ ጉዞ ዙሪያ ለቀረበለት ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ 10 ወር በጉዳት ተለይተህ አሁን ወደ ጨዋታው ተመልሰሃልና በጉዳት ወቅት የነበረህ ስሜት ምን ይመስላል….?
አይናለም፡- ከኳስ ርቆ መቆየት ለኔ ከባድ ነበር 10 ወር ሙሉ ጉዳት ላይ ሆኜ ሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ስታከም ነበርና ጊዜው ጥሩ ስሜት የፈጠረልኝ አልነበረም አሁን ግን እግዚአብሔር ይመስገን ያንን ሁሉ ረስቼ ወደፊት ማየት ጀምሪያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ላንተ ያላቸው ፍቅር ልዩ ነው.. ምክንያቱ ምን ይሆን?
አይናለም፡- በጣም የሚገርመኝ ጉዳይ ይሄ ነው የጎንደር ህዝብ ገራሚ ህዝብ ነው ለምን እንደሚወዱኝ አላውቅም፡፡ ምንም ነገር አላደረኩም ፍቅራቸው ግን ግርም ብሎኛል፡፡ በነበርኩበት ጊዜ የነበረኝ ትጋት ክብርና መወደድ አትርፎልኝ ከሆነ አላውቅም አሁን ድረስ የፍቅሩ ምንጭ አልገባኝም…. ወደፊት አደረኩ የምለው ነገር ቢፈጠር እንዴት ይወዱኝ ይሆን ብዬ አስባለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ወደ ምርጡ አቋምህ ገና አልተመለ ስክም…. ለዚህ ይሆን ቋሚ ያልሆንከው?
አይናለም፡- አዎ ገና ወደ ምርጡ አቋሜ አልተመለስኩም ገና ነኝ እየተቀየርኩ ነው የምገባው፡፡ በአጭር ጊዜው ቋሚ ተሰላፊ ለመሆን ጠንክሬ እየሰራሁ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ከፋሲል ከተማ ወቅታዊ አቅም ስናነሳ ዋንጫ ይጠበቃል?
አይናለም፡- ታድያስ? የምንጫወተውኮ ለዋንጫ ነው 2 ነጥብ ልዩነት ማለት የ1 ጨዋታ ውጤት ማለት ነው፡፡ በርትተን እንፋለ ማለን የሊጉ ዋንጫማ ጎንደር ይመጣል፡፡ ቀሪ 6 ጨዋታዎችን ትኩረት ሰጥተን በመጫወት ዋንጫውን እንደምናነሳ እርግጠኛ ነኝ፤ ፋሲል ከወትሮው ለየት ያለ ቡድን ሆኖብኛል ሻምፒዮን የሆነውን የ2005 የደደቢት ቡድንን ያስታውሰኛል፡፡ የአሰልጣኞቹ መናበብና መፈቃ ቀር እንዲሁም የቡድኑ ጥንካሬ ልዩ ነው የደጋ ፊው ስሜትማ የተለየ ነው፡፡ እንዲህ አይነት የአሰልጣኞች ቡድን አልገጠመኝም… ምክክሩ ግልፅ ነው የተጎዳ ተጨዋች በደንብ ክትትልና ድጋፍ ይደረግለታል፡፡ የሚገርመው እኔና ጀማል ጣሰው ነን ሲኒየሮች… ሁሉም ለኛ ያለው አመ ለካከት ነገን የሚያበረታን ሆኖልናል፡፡ የክለቡ አምበል ነኝ ተቀይሬ ስገባ አምበልነቱ የኔ ነው፡፡ ያን ያህል ክብር ተሰጥቶኛል ቡድኑን እያነቃቃሁ እያስተባበርኩ እገኛለሁ፡፡ ከዋንጫ አልፎ ኢን ተርናሽናል ጨዋታ የማድረግ ህልሙ አለን እንደሚሳካ አልጠራጠርም ደጋፊውም አመ ራሩም የምንፈልገውን አድርገዋል ከእኛ የሚጠ በቀው አሸንፎ ዋንጫ ማንሳት ብቻ ነው፡፡ ሌ ላው ክለብ ውስጥ የሚወራው ወሬ ፋሲል ው ስጥ አለመወራቱ ክለቡን የሚያስመሰግነው ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የዋንጫ ፉክክሩ በመቀለና ፋሲል ብቻ ነው ማለት ይቻላል?
አይናለም፡- እንደዚያ ማለት አይቻልም፡፡ ሲዳማ ቡናን ጨምሮ ሌሎችም አሉ ነገር ግን የኛ አቋም ጠንካራ በመሆኑ የተሻለ እድል እንዳለን ይሰማኛል በተከታታይ 4 ጨዋታ አሸንፈን ጉልበትና አቅም እያገኘን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የአዲስ አበባ ክለቦች ከዋንጫ ፉክክር ውጪ ናቸው ማለት ይቻላል?
አይናለም፡- አዎ በርግጥ በእግር ኳስ ርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም የአዲስ አበባ ክለቦች ከዋንጫ ፉክክሩ የራቁ ነው የሚመስለኝ…ተመልከት ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡናም ከኛ ርቀዋል፡፡ በኔ በኩል ከፋሲል ጋር ዋንጫውን አንስቼ ሁለተኛው የፕሪሚየር ሊግ ድሌ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ለፋሲል ከነማ ደጋፊዎች የምትለው ነገር አለ?
አይናለም፡- ለዋንጫ እየገሰገስን እንደመሆ ናችን ስንመራም ሆነ ስንመራ ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው…በጣም ነው የምወዳቸውና የማከብራቸው…. ጨዋታ ላይ ዝም ብለው የሚያዩትን አቁመው ሙሉ ድጋፋቸውን ሊሰጡን ይገባል፡፡ 90 ደቂቃ ደግፈውን ድላችንን በጋራ ልናከብር ይገባል ይሄ ቡድን እዚህ የደረሰው በነርሱ ነው ቀሪ 6 ጨዋታዎች ከጎናችን እንዲሆኑ አሳስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- ብዙዎች በቀሪ 6 ጨዋታ የፈሩት ተጋጣሚያቸው ሳይሆን ዳኝነቱን ነው.. አንተስ?
አይናለም፡- ውይ እሱማ ትልቅ ስጋት ነው አሁንኮ ነገሮች ከብደዋል በየክለሉ ያለው የስታዲ የሞች የፀጥታ ስጋት ካልተወገደ በቀጣይ ጉዟችን ላይ ስጋት ይፈጥራል… ለማንኛውም ዳኞች ለፍትህ የሚችሉትን ቢያደርጉ መልካም ነው እላለው፡፡
ሀትሪክ፡- ከደደቢት ጋር ስትጫወቱ ተመታህ አሉ…? አሁንስ ተሽሎሃል?
አይናለም፡- አዎ ከደደቢት ጋር በነበረን ጨዋታ አፍንጫዬና ጥርሴን በድንጋይ ተመትቼ ጥርሴን ለማስተካከል 2 ጊዜ ተነቅሻለው፡፡ ጀርባዬ ሁሉ አልቀረም፡፡ ይሄ አይነቱ ችግር በቀጣይ የሚያሰጋው ይሄ ነው፡፡ ኳሱ ቢቆም ይሻላል ነበር ያልኩት ከ1 ሰዓት በላይ ነው የቀጠቀጡን… ጎንደር ላይ መመታቴ ተሰምቶ ኖሮ እንዴት ተመታ ተብሎ ቀውጢ ተፈጥሮ ነበር… ወልዋሎን 1ለ0 ከረታን በኋላ ሲመለሱኮ የሸኘኋቸው ለዚህ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የወልዋሎ አዲግራትን የቡድን አባላት ኤርፖርት ድረስ ሄደህ ሸኘሃቸው…. ፈርተህ ነበር እንዴ?
አይናለም፡- በኔ መደብደብ ቁጣ ስለነበር ስጋት ነበረብኝ ነገር ግን የሚገርም አቀባበል ነው የተደረገላቸው… መቐለ ተመትቷል ተብሎ እዚህ ቢመቱ የት ሄጄ ልጫወት ነው ቀጥታ ወደ ቤቴ ነው የምሄደው ብዬ ተናግሬም ስለነበር በጥሩ አልቀባበልና በጥሩ አሸኛኘት ስፖርታዊ ጨዋታ በተሞላበት ሂደት በሠላም ተመልሰዋል፡፡ በዚህም ደስ ብሎኛል ደጋፊዎችን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡