“መቐለን በማሸነፋችን ዋንጫውን ማሰብ ጀምረናል” ሀብታሙ ገዛኸኝ (ሲዳማ ቡና) “ካሉት ጨዋታዎች አንፃር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ የማንሳት ዕድሉ በእኛ እጅ ነው ያለው” በዛብህ መለዮ /ፋሲል ከነማ/

በመሸሻ ወልዴ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ላይ የተካሄዱ ሲሆን በእለቱም ከተከናወኑት ግጥሚያዎች መካከል በከፍተኛ ጉጉት ተጠብቆ የነበረውን ጨዋታ ፋሲል ከነማ ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲን 1ለ0 እና ሲዳማ ቡና ደግሞ የሊጉን መሪ መቐለ 70 እንደርታን 2ለ1 በማሸነፍ ግጥሚያው ተጠናቋል፡፡
የፋሲል ከነማ ክለብ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት በመታጀብ ያደረገውን ጨዋታ 1ለ0 ያሸነፈው በበዛብህ መለዮ ብቸኛ ግብ ሲሆን ሲዳማ ቡና ደግሞ በሀብታሙ ገዘኸኝ እና በአዲስ ግደይ ግቦች መቐለ 70 እንደርታን ሊያሸንፉ ችለዋል፤ ለተሸናፊው ቡድን መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ቡድኑ በዜሮ ከመሸነፍ የዳነበትን ግብ አስቆጥሯል፡፡
የፋሲል ከነማ ክለብ የሊጉ መሪ የመቐለ 70 እንደርታን መሸነፍ ተከትሎም በመካከላቸው የነበረውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ያጠበበ ሲሆን ሌላው ድል የቀናው ሲዳማ ቡናም መቐለን ማሸነፉን ተከትሎ ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ማጥበብ ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን በማስመልከት ከእሁዱ ተጠባቂ ግጥሚያዎች መካከል ድል ከቀናቸው ክለቦች ውስጥ ለየቡድኖቻቸው ጥሩ ከመንቀሳቀስ በተጨማሪ ወሳኝ ግብ ያስቆጠሩትን ሁለት ተጨዋቾች ማለትም ከሲዳማ ቡና ሀብታሙ ገዛኸኝን እንደዚሁም ደግሞ ከፋሲል ከነማ በዛባህ መለዮን የሳምንቱ መጨረሻ ላይ ቡድኖቻቸው ድል ስላደረገበት ግጥሚያና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አናግረናቸው ምላሻቸውን እንደሚከተለው ሰጥተውናል፡፡

ሀትሪክ፡- የፕሪምየር ሊጉን መሪ መቐለ 70 እንደርታን 2ለ1 ለማሸነፍ ችላችኋል፤ ጨዋታው ምን መልክ ነበረው?
ሀብታሙ፡- የመቐለ 70 እንደርታ እና የእኛ የእሁዱ ጨዋታ በሁለታችንም መካከል ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ሲሆን በመጀመሪያ አጋማሽ ተጋጣሚያችን ይዞት ከቀረበው የመከላከል አጨዋወት አኳያ የእኛ ቡድን በከፍተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ ፕሬስ አድርጎ በመጫወቱ በኩል የተሻለ የነበረበት እና የድሉንም ጎሎች ያስቆጠረበት በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ መቐለዎች አጥቅተው ለመጫወት ሲሞክሩ እኛ ደግሞ የያዝነውን ውጤት አስከብሮ ለመውጣት በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ግጥሚያውን ያደረግንበት ስለነበር በዛ ተሳክቶልን ከሜዳችን ጣፋጭ የሆነ የማሸነፍ ድል ይዘን ልንወጣ ችለናል፡፡
ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታ ዘንድሮ ካለው ጥንካሬ አንፃር ጨዋታውን በድል እናጠናቅቃለን ብላችሁ አስባችሁ ነበር?
ሀብታሙ፡- አዎን፤ መቐለን እንደምናሸንፍ እርግጠኞች የነበርነው እነሱን ከመግጠማችን በፊት ነው፤ ሊጉ የ8 ሳምንታት ጨዋታዎች በቀሩበት ጊዜ በቡድናችን ዙሪያ በስፋት ተነጋግረን ነበርና ካሉን 8 ጨዋታዎች ውስጥ ቢያንስ 7ቱን ማሸነፍ አለብን ይህን ማድረግ ከቻልን ደግሞ ዋንጫውንም የምናነሳበት እድሉ አለን በሚል እቅድ ይዘን ስለነበር ነው መቐለንም አሸንፈን ከሜዳ ልንወጣ የቻልነውና ድሉ የሚገባን ጭምር ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡
ሀትሪክ፡- ክለባችሁ ሲዳማ ቡና መቐለ 70 እንድርታን ማሸነፉን ተከትሎ ከእነሱ ጋር የነበራችሁን የነጥብ ልዩነት ወደ 5 አጥብባችኋል፤ ከእዚህ በመነሳት የሊጉን ዋንጫ የማንሳት እድላችሁ የቱን ያህል ይሆናል?
ሀብታሙ፡- የመቐለ 70 እንድርታን ያሸነፍንበት ጨዋታ ለእኛ ሲዳማዎች ወደ ዋንጫው ፉክክር ውስጥ እንድንገባ ትልቁን የጥርጊያ መንገድ የከፈተልን በመሆኑ አሁን ላይ ምልከታችን ሁሉ ዋንጫው እና ዋንጫው ላይ ብቻ ነው፤ ይህን የሊግ ዋንጫ ለማንሳትም ቀሪዎቹ ጨዋታዎቻችንንም ወሳኞች ናቸውና እኛ ከዚህ በኋላ የራሳችንን የቤት ስራ ለመወጣት ብቻ ዝግጁ ነን፤ እንደ ቅርብ ጊዜ እቅዶቻችንም ከ8ቱ ጨዋታዎቻችን መካከል ከወዲሁ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ስላሸነፍንም ቀሪዎቹንም ግጥሚያዎች በስኬት በማጠናቀቅ የሊጉን ዋንጫ ለማግኘት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡
ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታ 48 ነጥብ፣ ፋሲል ከነማ 46 ነጥብ እንደዚሁም ደግሞ ሲዳማ ቡና 43 ነጥብ ነው ያላቸው፤ ይህን የተመዘገበ ውጤት ስትመለከት ዋንጫ ማንሳቱ ላይ ምንም አይነት ስጋት የለብህም?
ሀብታሙ፡- ብዙም አልሰጋም፤ ሲዳማ ቡና ከቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች መካከል ምን አልባት በጣም ሊከብደው የሚችለው ግጥሚያ ቢኖር ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በአዲስ አበባ ስታድየም የሚያደርገው ጨዋታ ብቻ ነው፤ ሌሎቹ ወጥቶ የሚጫወታቸው ጨዋታዎች ብዙ አያስቸግሩትም፤ የሜዳው ላይ ጨዋታን ደግሞ በማሸነፍ ጥሩ ሪከርድ ያለው ክለብ ስለሆነና ሁለቱ ከላይ የሚገኙት መቐለ 70 እንደርታና እና ፋሲል ከነማ ደግሞ በጣም ጠንካራ የሚባሉ ግጥሚያዎች በወራጅነት ቀጠናው ላይ ከሚገኙት ክለቦችም ጋር ጭምር ስለሚቀራቸው የእኛ ክለብ በራሱ ዕድል ላይ ብቻ በመወሰን የዘንድሮውን የሊግ ዋንጫ የሚያነሳበት እድሉ አለው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፉክክርን እንዴት ተመለከትከው?
ሀብታሙ፡- የዘንድሮው ፉክክር ትንሽ ከበድ ይላል፤ ከእዚህ ቀደም የአንድ ቡድን የበላይነት የሚታይበት ነበርና አሁን ያ ዘመን አልፏል፤ በዚህ ጊዜ ደግሞ በርካታ ክለቦች የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ቆርጠው የተነሱበት ስለሆነ ውድድሩም እያማረ ይገኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ሲዳማ ቡና መቐለ 70እንደርታን ሲያሸንፍ አንተ ያስቆጠርከው ግብ ለቡድናችሁ ወሳኝ ነበር፤ ጎል በማስቆጠርህ ምን አይነት ስሜት ተሰማህ፤ ከወቅታዊ አቋምህ ተነስተህስ በቀጣዩ ጊዜ ከአንተ ምን ይጠበቅ?
ሀብታሙ፡- ሲዳማ ቡና መቐለን ባሸነፈበት ጨዋታ እኔም ሆንኩ አዲስ ግደይ ለቡድናችን ያስቆጠርናቸው ግቦች ከወሳኝነታቸው ባሻገር የመጀመሪያዋ ግብም እኔ ያገባሁት በሊጉ መሪም ላይ ስለሆነ በግቧ የተሰማኝ የደስታ ስሜት ከፍተኛ ነበር፤ ያስቆጠርኳት ግብም በራሴ ላይ ያለኝን የተነሳሽነት ስሜት በጣም ጨምራልኛለችና በቀጣዮቹ ጨዋታዎችም ቡድኔን ለሻምፒዮናነት የሚያበቃ ውጤታማ ግልጋሎትን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ 1 ወልዋሎ አዲግራት 0 የሚል ውጤት ተመዝግቧል፤ ጨዋታው እንዴት ይገለፃል? ይህ ውጤትስ ምንን አመላክቷችኋል?
በዛብህ፡- የወልዋሎ አዲግራት ጋር የነበረን የእሁዱ ጨዋታ የሀገሪቱ ክልሎች ላይ አሁን አሁን በየጊዜው ከሚፈጠሩት የፖለቲካ ሽኩቻዎች አንፃርና በተለይ ደግሞ ከመሪው ክለብ መቐለ 70 እንደርታም ጋር በነጥብ የተቀራረብንበትና ኳሳዊ ባልሆኑ ጉዳዮችም ላይ የሁለቱ ቡድን ደጋፊዎች እና የክልሎቻቸው ነዋሪዎችም ልዩነትን በፈጠሩበት መልኩ ግጥሚያዎችን የምናደርግበት ጊዜ ላይ ስለሆንን ግጥሚያው ከበድ የሚል ነበር፤ ያም ሆኖ ግን በጨዋታው የእኛ ቡድን ብዙ የግብ እድሎችን በፈጠረበት ጨዋታ ላይ በእኔ ብቸኛ ግብ 1ለ0 አሸንፎ በመውጣቱ በጣም ደስ ሊለኝ ችሏል፡፡
ፋሲል ከነማ ወልዋሎን ያሸነፈበት ጨዋታ ለእኛ ያመላከተን ነገር ቢኖር ከመሪው ክለብ ጋር ያለንን የነጥብ ልዩነት ከማጥበቡ ባሻገር ዋንጫውንም እንድናነሳ እያቃረበን እና መንገዱንም እየከፈተልን ስለሆነም ይሄ ሌላው ደስተኛ ያደረገን ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- ለፋሲል ከነማ ጎል ማስቆጠር ችለሃል፤ ስለ ዘንድሮ የቡድኑ ተሳትፎ ምን ትላለህ? ቡድናችሁንስ እንዴት ትገልፀዋለህ?
በዛብህ፡- የፋሲል ከነማ ክለብ ውስጥ ያለኝን ቆይታ እንደ ቡድን ስገልፀው በጣም ጥሩ እና ደስ በሚል ስሜት ውስጥም ሆኜ ነው ራሴን የምመለከተው እንደ ግል ግን በበርካታ ግጥሚያዎች ላይ በቋሚ ተሰላፊነት ካለመጫወቴ አንፃር ብዙ ስኬታማ ተግባራቶችን በተደጋጋሚ ያልፈፀምኩ ስለሆነ ለወደፊቱ ከወልዋሎ ጋር ስንጫወት በማላውቀው የስኪመር ስፍራ ላይ ተጫውቼ የድል ጎል እንዳስቆጠርኩ ሁሉ ሌሎችም ብዙ የምሰራቸው ነገሮች ይኖራሉና ለዛ እየተዘጋጀው ነው የምገኘው፡፡
ሀትሪክ፡- የፕሪምየር ሊጉን ፉክክር እንዴት እየተመለከትከው ነው?
በዛብህ፡- የፕሪምየር ሊጉ ፉክክር ያልተጠበቁ ቡድኖች ዋንጫውን ለማንሳት እየተጫወቱ ከመሆናቸው አንፃር በጣም ጥሩ ነው፤ ከዚህ በፊት ለሊጉ የዋንጫው ፉክክር የሚጫወቱት ቅ/ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ነበሩ፤ አሁን ደግሞ የክልል ክለቦች ተጠናቅረው ስለመጡ እነሱ ለወሳኙ ዋንጫ እየተጫወቱ ይገኛልና ይሄ ሊጉን የተለየ አድርጎታል፡፡
ሀትሪክ፡- የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማን ያነሳል?
በዛብህ፡- የፕሪምየር ሊጉ ሊጠናቀቅ የ6 ሳምንታት ጨዋታዎች ቢቀሩትም የእኛ ክለብ ከሌሎቹ ተፎካካሪዎችም ሆነ ውድድሩን ከሚመራው መቐለ 70 እንደርታ ካለው ቀሪ ጨዋታ አኳያ የእኛ የተሻለ ስለሆነ ዋንጫውን የማንሳት እድሉ በእኛ እጅ ነው ያለው፤ ሻምፒዮናም እንሆናለን፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማን ለስኬት እያበቃው የሚገኘው ምንድን ነው?
በዛብህ፡- እንደ ቡድን መጫወታችን ከዛ ውጪ ደግሞ አሰልጣኛችን የሚሰጠን ልምምድ ጥሩ መሆኑና በተጨዋቾች ላይም ብቃታቸውን የሚጨምሩበትን ስልጠና ስለሚሰጥ ያ ጠቅሞናል፤ ሌላው ደግሞ ደጋፊዎቻችንም ተጨማሪ ኃይሎቻችን ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ….?
በዛብህ፡- የፋሲል ከነማ የዘንድሮ ቡድን ይለያል፤ ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብን ይዘናል፤ ጥሩም አሰልጣኝ አለን፤ ምርጥ ደጋፊዎችም አሉን ስለዚህ የሊጉ ዋንጫ ይገባናልና ይሄንን ለደጋፊዎቻችን ልናበረክት ተዘጋጅተናል፡፡

<p>Hatricksport website editor</p>

Facebook