Day: July 29, 2019

“የሚቀጥለውን የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ በመምራት ደስታውን የተነጠቀውን ሕዝቤን መካስ እፈልጋለሁ”ኢንተርናሽናል አልቢትር በአምላክ ተሰማ

 

  

ሀትሪክ፡- በቅድሚያ ለእኔም
ለአንባቢዎቼም ክብር በመስጠት ለጥያቄዎቼ
ምላሽ ስለሰጠኸኝ ከልብ አመሰግናለሁ…. ?
በአምላክ፡- …እኔም…አንተንም የሀትሪክ
ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልንም ከአንባቢዎች ጋር
የምንገናኝበት ድልድይ በመፍጠርህ ከልብ
አመሰግናለሁ…፡፡
ሀትሪክ፡- …የግብፁ የአፍሪካ ዋንጫ…
ግን…ቆይ…ቆይ…ከዚያ በፊት… ደፈርከኝ
እንዳትለኝ እንጂ… በአምላክ አንድ ጥያቄ
ልጠይቅህ ነው…?
በአምላክ፡- …(ሣቅ)…ለመጠየቅ አይደል
እንዴ የመጣሁት…?…ጠይቀኝ…?…(ሣቅ)…

ሀትሪክ፡- …አንተ በኢትዮጵያ ብቻ
አይደለም…በአለም ብሎም በአፍሪካ የታወክ
ትልቅ ክብርና ዝና ያለህ ኢንተርናሽናል
አልቢትር ነህ…ግን መኪና የለህም…በሰላም
ነው…?

በአምላክ፡- …(በጣም ሳቅ)…አዎን
የለኝም…!…(አሁንም ሣቅ)…

ሀትሪክ፡- …በአምላክ መኪና የማይገዛው
አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ “…ኦሎምፒክን
ካላሸነፍኩ መኪና አልነዳም…”እንዳለው
አንተም “…የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜን
ካልመራሁ መኪና አልነዳም…” ብሎ ነው
እስካአሁን መኪና ያልገዛኸው…ሲባል
ሰምቻለሁ…እውነት ነው…?

በአምላክ፡- …(በጣም ሣቅ)…ማነው ደሞ
እንደዚህ ያለህ…?…(አሁንም ሳቅ)…?…በጣም
ይገርማል…እኔ እንኳን መኪና ያልገዛሁት…
በተባለው ምክንያት አይደለም…(ሳቅ)…

ሀትሪክ፡- …ታዲያ በምንድነው…?…
በአቅም ነው እንዳልል…በዚህ አትታማም…
ታዲያ በምንድነው…?…እስቲ አንተው ራስህ
ንገረኝ…?
በአምላክ፡- …(አሁንም ያላባራ ሳቅ)…
በቃ እውነቱን ልንገርህ…?…(ሣቅ)…መንጃ
ፈቃድ ስለሌለኝ ብቻ ነው..(በጣም ሳቅ)…

ሀትሪክ፡- …መንጃ ፍቃድ እስከአሁን
አላወጣህም…?

በአምላክ፡- …እውነት ለመናገር መኪና
መግዛቱ አይደለም የከበደኝ የህጋዊነት
ጉዳይ ነው እስከአሁን መኪና ከመንዳት
ያገደኝ…፤…አሁን ግን መኪና የቅንጦት
ሣይሆን ግዴታ እየሆነ የመጣበት ዘመን ላይ
ስለደረስን የመግዛቴ ነገር ግድ ሆኗል…፡፡
…ግን ከመኪናው በፊት መቅደም ያለበት
መንጃ ፍቃድ ስለሆነ በሥርዓት ተምሬ መንጃ
ፍቃዴን አውጥቼ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ
ስሽከረክር ልታየኝ ትችል ይሆናል…(በጣም
ሳቅ)….

ሀትሪክ፡- …አሁን ወደ ግብፁ የአፍሪካ
ዋንጫ እናምራ እስቲ…ግን…ቆይ…ቆይ…
ይሄንንም ጥያቄ አሁንም ላቆየውና…ከዚያ
በፊት…ሁሌም ግርም ስለሚለኝ አንድ ነገር
ልጠይቅህ…?

በአምላክ፡- …(ፈገግ እንደማለት እያለ)
…ደሞ ምን ልትለኝ ይሆን…?…(አሁንም
ሳቅ)…

ሀትሪክ፡- …በአምላክ አለበበስ ላይ
ሣይህ ብዙም ግድ የለሽ ሰው ትመስለኛለህ…
ተሳሳትኩ…?
በአምላክ፡- …(ኮስተር እንደማለት ብሎ
ፊቱን ጨምደድ አድርጎ)…ከምን መነሻነት
እንዲህ ልትል ቻልክ…?

ሀትሪክ፡- …አይ ብዙ ጊዜ ሳይህ…ሱፍ
ለብሰህ ሣይሆን…ቱታና ከላይ ኮፊያ ያለውን
አላባሽ ጣል አድርገህ ስለሆነ…ከዚያ በመነሳት
ነው ይሄንን ጥያቄ ያነሳውልህ…ምነው…
አጠፋሁ…?

በአምላክ፡- …(መሳቁን አላቋረጠም)…
አንተ የምትገርም ሰው ነህ…ለነገሩ እውነትህን
ነው…በጣም ግድ ካልሆነ በስተቀር ሙሉ ሱፍ
መልበስ ብዙም አይመቸኝም…፤…በጣምም
ያጨናንቀኛል…።…ከእሱ ይልቅ ቀለል ያለ
አለባበስ ምርጫዬ ነው…፤…እንዳልከው
ቱታና ከላይ ኮፍያ ያለው አላባሽ እላዬ ላይ
ጣል አድርጌ መሄድን ሁሌ የማስቀድመው…
(ሣቅ)…

ሀትሪክ፡- …አንዳንዶች ደግሞ…አይናፋር
ስለሆነና…ትኩረት ላለመሳብ ነው ለአለባበሱ
የማይጨነቀው ሱፍ የማያዘወትረው
ይሉሃል…?

በአምላክ፡- …(አሁንም ሣቅ)… ወይ
ጉድ…ትኩረት ላለመሳብ…?…አይናፋር
ስለሆነ…?…(በጣም ሳቅ)… ይሄንን እንኳን
አልቀበለውም…፤…15 እና 20 ሪከርዶችን
የሰባበሩ በርካታ ታላላቅ ታሪኮችን የሠሩ
አትሌቶችና ሰዎች ያሉባት ሀገር እኮ ናት
ሀገራችን…እኔ ገና አንድ የቻምፒዮንስ ሊግ
ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታዎችን ወይም የአፍሪካ
ዋንጫ ጨዋታን ስለመራሁ ሱፍ አድርጌ
እዩኝ እዩኝ ብዬ ከተማዋን ባጣብብ መልካም
ይሆናል ብዬ አላሰብም…፡፡…ሀገራችን
የስፖርተኞች፣የታሪክ ሠሪዎች ሀገር ናት…
እንደዚህ አይነት ሰዎች ባሉበት ሀገር…ራሴን
መደበቅ ወይም እነሱ የሠሩትን ስኬታቸውን
መከተል እንጂ…መታየትን አላስቀድምም…
ያ ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- …በዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ
ላይ በርካታ ጨዋታዎችን በመምራት
የመጀ sመሪያው ኢትዮጵያዊ ለመሆን
በቅተሃል…፤…ከዚህ ውጪ የአፍሪካ
ቻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታን፣በርካታ
የክለቦች ውድድሮችን እንዲሁም ለዋናው
የአለም ዋንጫ የተመረጥክ የመጀመሪያው
ኢትዮጵያውያ ሆነሃል ከዚህ አንፃር ይሄ
አመት የበአምላክ አመት ነው ብሎ መናገር
ይቻላል…?

በአምላክ፡- …(ፈገግ እንደማለት እያለ)…
እውነት ለመናገር አዎን ማለት ይቻላል…፤…
በቅድሚያ ይሄ እንዲሆን የፈቀደው አምላክ
ምስጋና ይግባውና…በዚህ አመት ስኬታማ
የሚባሉ ጊዜያትን፣በሙያዬ ታላላቅ ታሪኮችን
ማፃፍ የቻልኩበት አመት ነበር…፡፡…
በእስከዛሬው የዳኝነት አመታት በተሻለ ከፍ
ብዬ የታየሁበት አመት በመሆኑ የእኔ አመት
ነበር ብል ለራሴ ያዳላሁ…አንባቢም ቅር
የሚለው አይመስለኝም…(ሣቅ)…

ሀትሪክ፡- …እስቲ አሁን ወደ ዋናው
ጉዳያችን እንግባ…የዘንድሮው የግብፁ
የአፍሪካ ዋንጫን እንዴት አገኘኸው…?…
ፉክክሩ፣ድምቀቱ…በአንተ አንደበት እንዴት
ይገለፃል…?

በአምላክ፡- …በጣም ጥሩ የሚባል
የአፍሪካ ዋንጫ ነበር…፣…ፉክክሩም
በጣም መልካም የሚባል ነው፡፡ ያልተጠበቁ
ቡድኖች የታዩበት…ብዙ የተጠበቁ ደግሞ
ባልተጠበቁ ቡድኖች ተሸንፈው ብዙ
ርቀት ሳይጓዙ መንገድ የቀሩበት…በአጭሩ
የፉክክር መንፈሱ የማይገመት ነበር ማለት
ይቻላል፡፡ በዚህ በኩል ያለው ነገር መልካም
ቢሆንም የተመልካች ማነስ ውድድሩ የበለጠ
እንዳይደምቅ ያደረገውም ይመስለኛል፡፡
በተለይ አዘጋጅዋ ሀገር ግብፅ ከውድድሩ በጊዜ
መውጣቷ ስታዲየሞች በተመልካች ድርቅ
እንዲመቱ የስታዲየሙ ድባብም እንዲደበዝዝ
ከማድረጉ ውጪ በጣም ጥሩ የአፍሪካ ዋንጫ
ነበር ማለት ይቀለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- …አልጀሪያ የውድድሩ አሸናፊ
ሆናለች…ይገባታል…?

በአምላክ፡- …አልጄሪያዎችን እንደ
አጋጣሚ ሆኖ የማጫወት እድሉ ገጥሞ
ኛል…፤ … ከዚህ ውጪም ቡድኑ ሲጫወት
የመመልከት እድልም አጋጥሞኝ በጣም
ጠንካራና ለሻምፒዮናነት የተሠራ ብ/
ቡድን እንደሆነ ለመገመት አልተቸገርኩም፡
፡ ከውድድሩ በፊትም ዋንጫውን ያለስስት
የሰጠሁት ለዋንጫ ያጫሃቸው አልጄሪያዎችን
ነው…፤…የቡደኑ አገነባብ…፣…
የቡድኑ ስብስብ…፣…የተጨዋቾች የላቀ
ክህሎት…፣…በተጨዋቾች ላይ የሚነበበው
የአሸናፊነት ስሜትን ልብ ብለህ ስትመለከት
ብቸኛ ምርጫህ ለዋንጫ ማጨት ብቻ
ነው…፤…በእኔ እምነት ጥሩ ቡድን የአፍሪካ
ዋንጫውን አሸንፏል…፡፡

ሀትሪክ፡- …በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ
ከእስከዛሬ በተለየ ሁኔታ ጋና ከካሜሮን፣
ኮትዲቯር ከአልጄሪያ፣ ሴኔጋል ከቱኒዚያ
ያደረጉትን ታላላቅና ወሳኝ ጨዋታዎችን
መርተሃል…፤…ይህ መሆኑ ካፍ በአንተ ላይ
ያለው እምነት…ከፍ ማለቱን የሚያሳይ
ነው…?

በአምላክ፡-…ኧ… እንግዲህ…በአንድ
እግር ኳስ ተሰላፊ (ቤስት 11) ውስጥ ለመግባት
ፉክክርን ይጠይቃል…፤…በዳኝነትም የተሻለ
ጨዋታን ለመምራት መፎካከር ይጠብ
ቅብሃል…፡፡…ለእንደዚህ አይነት ታላላቅ
ውድድርም ተመርጠህ በምትሄድበት ጊዜ
ከሌላ ሀገር ከመጡ ዳኞች ጋር ስፖርታዊ
ፉክክር ማድረግን ይጠበቅብሃል…፡፡…እኔም
ልክ እግር ኳስ ተጨዋቾች ቋሚ ተሰላፊነትን
(ቤትስ 11) ውስጥ ለመግባት የሚያደርጉትን
ፉክክር በዳኝነቱም በሚገባ አድርጌያለሁ፡፡
በእንደዚህ አይነት ቶርናመንቶች ላይ ከኋላ
የሠራኋቸው መልካም ነገሮች ለዛሬው እንደ
አንድ ክሬዲት አይያዙልህም፤ ምናልባት
እንደ አንድ ያለፈ ኤክስፒሪያንስ ነው
የሚሆንህ…።…ፉክክሩን አሸንፈህ ተመራጭ
ለመሆን የቅድመ ውድድር ትሬይኒንግ ላይ
መስራት ማሳየት አለብህ…፤…እኔም ያንን
ፉክክር በሚገባ ለማድረግ ሞክሬያለሁ…፡፡…
ደግሞም እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን…
ያደረኩት ፉክክር ተሳክቶልኛል ማለት
እችላለሁ…፡፡

ሀትሪክ፡- …ከመራሃቸው ታላላቅ ጨዋታ
ዎች… የተሻለ የነጥብና አስተያየት ያገኘህበት
ጨዋታ የትኛው ነው…?

በአምላክ፡- …በአብዛኛው ሁሉም ጥሩ
ናቸው ማለት ይቻላል…፤…ከፍተኛውንና
ጥሩውን ግምገማ ያገኘሁት የሩብና የግማሽ
ፍፃሜ ላይ በመራኋቸው ጨዋታዎች ላይ
ነው…፡፡…ከእነዚህ ጨዋታዎች በፊት
የነበረው የካሜሮንና የጋና ጨዋታም መልካም
የነበረ ቢሆንም በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ
ላስተካክላቸው የነበሩ ነገሮች የተነገሩኝ…
እኔም የተቀበልኳቸው ናቸው…፡፡

ሀትሪክ፡- …በፍጥነቱ፣በፉክክር ስሜ
ቱም፣ በቴክኒኩ በኩል የፈተነህ ጨዋታስ…?

በአምላክ፡- …ኦው…!…የአልጄሪያና የአ
ይቮሪኮስት ጨዋታ ነው…፡፡…የመሸናነፍ
ፉክክሩ በ90 ደቂቃ ያልተገደበ…120 ደቂቃም
ያልፈታው…የተለየ የፉክክር ስሜት…፣…
የማሸነፍ ረቂቅ ጥበብ የታየበት እኔም
እያንዳንዷን የጨዋታ እንቅስቃሴ ለመከታተል
በጣም ያሯሯጠኝ ጨዋታ ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …በዚህ ጨዋታ ብዙ ኪሎ
ሜትሮችን በሩጫ ማካለልህን ነው የሠ
ማሁት…ትክክል ነኝ…? …ለመሆኑ ስንት ኪሎ
ሜትር ሸፍነሃል…?

በአምላክ፡- …በጣም የሚገርምህ ከመራ
ኋቸው ብቻ ሣይሆን ከቶርናመንቱ፣ከሁሉም
ዳኞች ጭምር ከፍተኛ ኪሎ ሜትር በሩጫ
የሸፈንኩበት ትልቀ ጨዋታም ሆኖ ነው
የተመዘገበው፡፡ በጣም የሚገርምህ በአልጄሪያና
አይቮሪኮስት ጨዋታ 14.30 ኪሎ ሜትር ነው
በሩጫ የሸፈንኩት በእርግጥ ጨዋታ 120
ደቂቃ ድረስ የዘለቀ ቢሆንም ከውድድሩ ይሄን
ያህል ኪሎ ሜትር የሸፈንኩበት በትልቅነትም

የተመዘገበ ጨዋታ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ብዙዎች ጉዳዩን ለማወቅና
ከአንተ ለመስማት ስለሚጓጉለት የሴኔጋልና
ቱኒዚያ ጨዋታ ከሳዲዮ ማኔ ጋር ስለነበረ
አንድ ክስተት ልጠይቅህ…፤…በዚህ ጨዋታ
ከሳዲዮ ማኔ ጋር ትሳሳቁ እሱም በወንድማዊ
ፍቅር ወገብህን እየነካ ፈገግ ስትሉ ስትሳሳቁ
በቴሌቭዥን መስኮት ታይቷችሃል…?…ምን
ተባብላችሁ ነው ስትሳሳቁ የነበረው…?
በአምላክ፡- …(ሳቅ)…ሳዲዮ ማኔ
ትልቅ ፕሮፌሽናል ተጨዋች ነው…፤…ይህ
ተጨዋች አለም ውስጥ ካሉ ቁጥር አንድ
ተጨዋች ነው…፡፡…ከችሎታው በላይ በጣም
ጨዋ ዲሲፒሊን የሚያከብር ትልቅ ተጨዋች
ነው…፡፡…በዚያች ቅፅበት አንዳችን ለአንዳችን
ያለንን ክብርና ፍቅር ነው የተገላለፅነው…፤…
በአጭሩ እንደምንዋደድ…አንዳችን ለአንዳችን
ትልቅ ቦታ እንዳለን ነው…በፍቅር…
በወንድማዊ ስሜት…ነው…በዚያች ቅፅበት
የተገላለፅነው…፡፡…በነገራችን ላይ ማኔ
ከእኔ ጋር ብቻ ሣይሆን ከሁሉም ዳኞች
ጋር ተግባብቶ ስራውን የሚሠራ ጨዋ ልጅ
ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …ከሳዲዮ ማኔ ሌላ…
በሀገራችን በርካታ አድናቂዎች፣አፍቃሪዎች
ያላቸው የአርሴናሉን ኮከብ ናይጄሪያዊውን
አሌክስ ኢዎቢ፣የአልጄሪያው ሪያድ ማሀሬዝን
የመሳሰሉ ኮከቦችም የማጫወትና እነሱንም
በቅርበት የማግኘት እድል አግኝተሃልና ከእነሱ
ጋር የነበረው ሁኔታ…?

በአምላክ፡- …እንግዲህ እነዚህን
የመሳሰሉ በሀገራችንም በአለምም ትልቅ
አድናቂ ያላቸውን ተጨዋቾች ማጫወት የተለየ
ስሜት በውስጥህ እንዲፈጠር ያደርጋል…፡፡…
እንደእነዚህ አይነት ተጨዋቾች ፕሮፌሽናሎች
በመሆናቸው በአብዛኛው ሥራቸውን
እንዴት መስራት እንዳለባቸው ስለሚያውቁ
አንዳችን አንዳችንን ከማድነቅ በስተቀር
በተለየ ውሳኔዎችን ተከትሎ
የተነጋገርንበት ሁኔታ
የለም…፡፡ ያም ቢሆን ግን
ከሪያድ ማሀሬዝ ጋር
የተወሰነች ደቂቃም ቢሆን
ያወራንበት አጋጣሚ ነበር፡
፡ የጨዋታው ሂደት ጥሩ
ስለነበር ውይይቶቻችንና
ግ ን ኙ ነ ቶ ች ቻ ች ን ም
መልካም ነገር ላይ ያተኩሩ
ነበሩ፡፡ ከዚህ ሌላ ግን
አንድ ማንሣት የምፈልገው
በግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ የሴኔጋል
ብ/ቡድን አምበል ቀደም
ብሎ ቢጫ ካርድ
አግኝቶ ነበር
ተጨማሪ ካርድ ካየ የፍፃሜ
ጨዋታ ያመልጠዋል፤በዳኝነት
18ኛውን common sense ይሄ
ማለት ፕሪቬ ንሽን አንድ ነገር
ከማድረግህ በፊት የሚለውን
መምህሮቼ ያስተማሩኝን
በማስታወስ መነካካት ደረጃ…
ቅርብ ለቅርብ በመፋ ጠጥ ደረጃ
ተነጋግረንበት እሱም ፕሮፌሽናል
በሆነ ሜንታሊቲ የተቀበለበት
የእኔም የመከላከል ስራዬም
መልካም የሆነበት ሁኔታን ነው
የማስታውሰው፡፡
ሀትሪክ፡- …እነዚህን
የአለማችን ታላላቅ ኮከቦች
በቴሌቪዥን መስኮት
ሲታዩ በጣም ገዝፈው ነው
የሚታዩት…፤…አንተ እነ ማኔን
በአካል ሜዳ ውስጥ ስታያቸው
ከቴሌቪዥኑ ጋር ያላቸው
አንድነትና ልዩነት ምንድነው…?
በአምላክ፡- …እዚህ
ላይ አንተም ብዙ ታላላቅ
ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን
በአካል ተገኝተህ ተከታትለህ
እንደታዘብከው ነው እኔም
የታዘብኩት…፤…በቴሌቪዥን
መስኮትና በአካል ሲታዩ የተለያዩ
ናቸው፤በቴሌቪዥን ትንሽ
የመግዘፍ ነገር አለ፡፡ ሳዲዮ ማኔ
እንኳን ብዙ የተለየ የተጋነነ
ነገር አላየሁበትም…ከእሱ ይልቅ
አይቼው በጣም የተገረምኩት
በሪያድ ማሀሬዝ ነው…፤…ሪያድ
ማሀሬዝ በዚህ ደረጃ በጣም
ቀጥኖና ረዝሞ አየዋለሁ ብዬ
አላሰብኩም ነበር…፤…እሱ ላይ
የተጋነነ ነገር አይቼበታለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …እኔን
ጨምሮ በርካታ
ኢትዮጵያዊያን
የአፍሪካ ዋንጫ
የፍፃሜ ጨዋታ
በሀገራችን ልጅ
ሲመራ ለማየት
በጣም ጓጉተን
ነበር…መጨረሻ
ላይ ምኞታችንን
የሚያጨናግፍ ነገር ተከሰተ
እንጂ… አንተስ ይሄንን ነገር
ጠብቀህ ነበር…?
በአምላክ፡- …(ፈገግ ብሎ)…
ሁለት ነገር ነው በውስጤ
የ ነ በ ረ ው … ፤ …

በአፍሪካ ዋንጫው የሩብ ፍፃሜን ሳጫውት
አይ ዘንድሮስ የፍፃሜው ጨዋታ ሊሰጠኝ
ወይም ልመራው እችል ይሆናል ብሎ የማሰብ
ሁኔታ በውስጤ ይኖራል፡፡ ግን ሩብ ፍፃሜውን
ከመራሁ በኋላ እንደገና ግማሽ ፍፃሜውን
እንድመራ እድሉ ሲሰጠኝ አይ ይሄ ነገር ላይሳካ
ነው እንዴ? የሚል ሌላ ሃሳብ ደግሞ በውስጤ
ተፈጠረ፡፡ ምክንያቱም በእግር ኳስ በአብዛኛው
ሩብ ፍፃሜውን አጫውተህ እንደገና ግማሽ
ፍፃሜውንም ደግመህ የዋንጫውን ጨዋታ
የማጫወት እድሉ የጠበበ ነው…፤…በዚህ
የተነሣ ግማሽ ፍፃሜው ሲሰጠኝ ምናልባት
ፍፃሜውን ላልመራ እችላለሁ ወደሚል ነገር
ወሰደኝ…ነገር ግን አብሮኝ ከነበረው ረዳት ዳኛ
ጋር በዚህ ዙሪያ ስናወራ “…አይ አንዳንዴ
በእግር ኳስ እንደዚህ ይከሰታል…፤…
ሩብና ግማሽ ፍፃሜውን የመራ የዋንጫ
ጨዋታውንም ሊመራ በተለየ ሁኔታ እድሉን
ሊያገኝ ይችላል…”…በማለት አባባሉን
በዳታ ጭምር አስደግፎ ሲያሳየኝ…እንደገና
ሃሣቤን እንድለውጥ…የፍፃሜውን ጨዋታ
እውነት እንዳለው ልመራ የምችልበት እድል
ሊኖር ይችላል ብዬ እንዳስብ አደረገኝ…፤…
ግን ያው ሰው ያሰበው ሣይሆን አምላክ
ያለው ነው የሚሆነው…በቃ…መጨረሻ ላይ
አልተሳካም…(ሳቅ)…፡፡
ሀትሪክ፡- …አንተ የፍፃሜውን ጨዋታ
እንደምትመራ በተለያዩ የሀገራችን ሚዲያዎች
በመዘገቡ ህዝቡ በተለይ የስፖርት ቤተሰቡ
ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፍን…ከዚህ ከፍ ሲልም
የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳን ያህል በጣም
ተደስቶ…ስሜቱን በተለያየ መንገድ ሲገልፅ
ነበር…ይሄንን ነገር ታውቅ ትከታተል ነበር…?

በአምላክ፡- …(ፈገግ ብሎ)…አዎን
በጣም እከታተል በተለያየ ነገር እሠማ
ነበር…፤…ይህ ሁኔታም ሁለት የተዘበራረቀ
ስሜትን በውስጤ ፈጥሮ ነበር…፡፡…
አንደኛው የህዝቡ በዚህ ደረጃ ደስታውን
መግለፅ…የማላውቀው የደስታ ስሜት
በውስጤ እንዲፈጥር ቢያደርገውም…ዜናው
ገና ያልተረጋገጠና በይፋ ያልተገለፀ ነገር
በመሆኑ…የህዝቡ ስሜት እንዳይጎዳ በተለያየ
መንገድ ለማረምም እሞክር ነበር…፡፡…
ሌላው ያ ህዝቡ የተመኘው፣የጓጓለት ነገር
ለጊዜው ተሳክቶ አብረን መደሰት ባንችልም
አጋጣሚው ግን አንድ ትልቅ ቁም ነገር
ያለው መልዕክት አስተላልፎልኝ፣ ድርብ
ድርብርብም ኃላፊነትም ሰጥቶኝ አልፏል…፡
፡…አጋጣሚው ለእኔ ብቻ ሣይሆን ወደፊት
በዳኝነት፣በአትሌትነት፣ በተጨዋችነት፣በብ/
ቡድን ደረጃ በተናጠልም በቡድንም የሀገርን
ስም ማስጠራት፣ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድ
ነገር ማሳየት ማለት ምላሹ ምን ያህል ትልቅ
እንደሆነ በግልፅ አይቼበታለሁ፡፡ ለካ ብቻዬን
አይደለሁም…የኢትዮጵያ ህዝብ በእያንዳንዱ
እንቅስቃሴዬና ስኬቴ ጀርባ አለ እንድልም
አድርጎኛል…፡፡


ሀትሪክ፡- …ግን መጀመሪያ ላይ ህዝቡን
በዚህ ደረጃ ጠብቀኸው ነበር…?
በአምላክ፡- …በዚህ ደረጃ…?…ኧረ…
በፍፁም…አልጠበኩም…!…የአፍሪካ ዋንጫን
መከታተል ያልቻልበት ምቹ ያልሆነ ሁኔታ
ውስጥ ሆኖ…የአንድ ሰው የሀገር ውክልና
በዚህ ደረጃ ትልቅ ትኩረትና ዋጋ ይሰጠዋል..
ደስታውም እንደሀገር ይሆናል ብዬ በዚህ
ደረጃ አልጠበኩም…።…እዚህ ከመጣሁ በኋላ
የሰማሁት ለማመን የሚከብድ ሆኖ ነው
ያገኘሁት…፤…በዚህ አጋጣሚ ይሄን ውለታን
የሚያውቅ…፤… ልፋትን የሚቆጥር ህዝቤን
ከልብ ማመስገን እወዳለሁ…፡፡
ሀትሪክ፡- …የህዝቡ ስሜት እንዲህ
በጋለበት…ጨዋታውን ስትመራ ለማየት
በጉጉት እየጠበቅህ ባለበት ሁኔታ…
ጨዋታውን እንደማትመራ ስታውቅ
በውስጥህ ምን ተፈጠረ…?
በአምላክ፡- …በቃላት መግለፅ
የማልችለው የቁጭት ስሜት ነው በውስጤ
የተፈጠረው…፤…እውነቱን ልንገርህ ከእኔ
ይልቅ በጣም ያንገበገበኝ በዚያ የተቀጣጠለው
የህዝቡ ስሜት ላይ ምን ሊፈጠር
ይችላል…?…የሚለው ሳስብ ነው…፡፡…ህዝቡ
ገና ጨዋታውን ሳልመራ እንደዚህ የሆነ
ስመራ ሲያይ ምን ሊከሰት ይችላል…?…
ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሣላገኝ ጨዋታውን
እንደማልመራው ሲታወቅ የተቀጣጠለው
የደስታ ስሜት ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ሲቸለስበት
ታየኝ…፡፡…በዚህ የተነሣ ነገሩን ለመርሳት
ወይም በሌላ ነገር ለማስታወስ በማሰብ
ጅምናዚያም እየሠራው ማሳለፍን ነው
የመረጥኩት…በቃ…ወደ ሌላ ወደማላውቀው
ቁጭትና ቁጣ ልበለው…ወደዚያ ነው
የከተተኝ…፤…ይሄ ህዝብማ ደስታውን ተነጥቆ
አይቀርም ብዬ…ጅምናዚየም ውስጥ ከዚያን
ቀን ጀምሮ ነው መስራት የጀመርኩት…፡፡

ሀትሪክ፡- …የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜን
ለመምራት ለበአምላክ ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ
ወይም እድል የለም…፤…አሁን ካልመራ
ከዚህ በኋላ ይቸገራል…የሚሉ አሉ…አባባሉን
ትቀበለዋለህ…?

በአምላክ፡- …ዳኝነት ፉክክር ነው…፤…
የተሻለ የዳኝነት ፉክክር ያደረኩበት…ራሴን
በአግባቡ ያሳየሁበት…ታላላቅ የሚባሉ
ጨዋታዎችን የመምራት እድል ያገኘሁበት
ጊዜ እንደሆነ ግልፅ ነው…፡፡ ዕውነት ነው
በተሻለ መልኩ ፉክክር አድርጌያለሁ…፤…
ግን ከዚህ በመነሣት የፍፃሜ ጨዋታውን
ለመምራት ትክክለኛው ጊዜ ነበር…
አልነበረም ብዬ እኔ ራሴ ለራሴ ፍርዱን
ከምሰጥ…ለተመልካቹ ወይም ይሄንን
ፉክክር ለሚዳኙት አካል መተው የተሻለ
ነው ብዬ አስባለሁ…፡፡…በእኔ አመለካከት
የተሻለ ለመሆን ተፎካክሬያለሁ…፤…ከዚህ
ያለፈውን ለሚመርጠው አካል ብንተወው
ነው የሚመረጠው…፡፡…እንደ እኔ ግን
ከነበሩት ሲኒዬር ዳኞች አንፃር በዚህ ደረጃ
እርግጠኛ መሆን አይቻልም…፤…ከጓደኞቼ
ጋር በጋራ በመሆን የሆነ ነገር ለማሳየት
ሞክሬያለሁ…፡፡…ከእኔ በላይ ሲኒዬር የሆኑ
ዳኞች አሉ…፤…ግን ፉክክሩ ሲጀመር እኔም
እንደማንኛውም ቤስት ውስጥ ለመግባት
እንደሚፈልግ ተጨዋች የተሻልን ሆነን
ለመመረጥ ፉክክር ለማድረግ ሞክሬያለሁ…
ያም የተሳካ ነበር ለማለት እችላለሁ…የምለው
ይሄንን ነው…፤…ከዚህ ውጪ የፋይናሉን
ጨዋታ ለመምራት ትክክለኛው ጊዜ ይሄ ነበር
የሚያስብል ነገር የለም…፡፡
ሀትሪክ፡- …ከዚህ በኋላስ…በአምላክ
የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜን ስለመምራት
ያስባል…?…ይመኛል…?
በአምላክ፡-… ( ሳ ቅ ) … እ ን ዴ … ም ን
ማለትህ…ነው…?…በጣም አስባለሁ…
በጣምም እመኛለሁ…፤…እንደውም ቁርጥ
ያለው ምኞቴን ልንገርህ..?…(ሳቅ)…
የሚቀጥለውን 33ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ
መምራት ያለብኝ እኔ ነኝ ብዬ ለራሴ ቃል
ገብቼ ዝግጅት የጀመርኩት ወዲያውኑ
ነው…፡፡ በህዝቡ ላይ ያየሁት ስሜት ይሄን
የግድ ለማሳካት ከወዲሁ ጠንክሬ መስራት
እንዳለብኝ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የህዝቡን
ስሜትና ፍላጎት አለማሳካቴ በውስጥ የቁጭት
እሳት እንዲቀጣጠል አድርጓል፡፡ ከዚህ አንፃር
ቀጣዩን የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ መምራትን
በጣም ነው የምመኘው፤ ከእኔ ምኞት ያለፈ
ያለውን እውን የሚያደርገው የፈጠረኝ
አምላክ ነው፡፡ ምኞቴ ተገቢ ነው ከዚህ በኋላ
የሚሆነውን አብረን ለማየት ያብቃን ነው
የምለው…፡፡
ሀትሪክ፡- …በግብፅ ቆይታህ በተለይ
ከኢትዮጵያውያን የገጠመህ የተለየ አጋጣሚ
ነበር….?
በአምላክ፡- …በግብፅ የሚኖሩ
ኢትዮጵያውያን እኔንም ረዳት ዳኛውን
ተመስገንን መጥተው አነጋግረውናል…፤…
ሀገራችንን ወክለን በመገኘታችን
ደስተኞች እንደሆኑ እንደኮሩብን ገልፀው
አ በ ረ ታ ተ ው ና ል … ፤ … ኢ ት ዮ ጵ ያ ዊ
ፍቅራቸውንና ድጋፋቸውን ለግሰውናል፡
፡ የመራናቸውን ጨዋታዎች እንደተመለከቱ
በዚህም ደስተኞች እንደሆኑም እንደዚሁ
ገልፀውልናል፡፡ ከዚህ ውጪ በግብፅ የኢትዮጵያ
ኤምባሲ አምባሳደር ክብር አምባሳደር ዲና

ሙፍቲም የኤምባሲው ሰዎችም ሆቴል ድረስ
መጥተው አግኝተውናል…፤… ሀገራችንን
ወክለን በዚህ የአህጉሪቱ ትልቅ ውድድር
ላይ በመገኘታችን ስፖርታዊ ተልዕኮአችን
መልካም መሆኑን በመገንዘብ የክብር ግብዣና
ምስጋና አቅርበውልናል፤አበረታተውናል፡
፡በዚህ አጋጣሚ ክብር አምባሳደሩንም
የኤምባሲውን የቆንስላ ሠራተኞች እንዲሁም
በግብፅ ያገኘናቸውን ኢትዮጵያውያን ከልብ
ለማመስገን እወዳለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …“ኢትዮጵያ” የሚለው ታላቅ
ስም በአንድ በአምላክ…በአፍሪካ መድረክ
ላይ ከፍ ብሎ መጠራቱ እንደ አንድ ዳኛ ምን
ስሜት ፈጠረብህ…?


በአምላክ፡- …ሀገር በስፖርት ውድድር
ውስጥ ስሟ ከፍ ብሎ የሚጠራው በአትሌቲክስ
ወይም በእግር ኳስ በብ/ቡድን ነው…፡፡…ብ/
ቡድናችን በዚህን መሠሉ መድረክ ላይ ተገኝቶ
የሀገራችን ስም ሲጠራ ማየት ከምንም በላይ
ያስደስት ነበር፡፡ እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ
እንደ አንድ የስፖርት ባለድርሻ የኢትዮጵያ
ብ/ቡድን ሣይ ከፍተኛ የደስታ ስሜት ነው
የሚሠማኝ፡፡ ይሄ ሣይሆን ቀርቶ በአንድም
ይሁን በሁለትና ሶስት ባለሙያ የመወክል
እድል አግኝታ ስምዋ መጠራቱም መፅናኛ ብቻ
ሳይሆን ትልቅ የደስታ ስሜትንም ይፈጥራል፡
፡ በዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ሀገራችን በሁለት
ኢንተርናሽናል ዳኞች እንዲሁም የብ/ቡድኑ
ዋና አሰልጣኝም ነበር…በዚህ መንገድ
መወከልዋና መሣተፏ ብሎም “ኢትዮጵያ”
የሚለው ስም መጠራቱ ለሙያተኞች
የሀገራቸውን ስም የሚያስጠሩበት…
ለራሣቸውም ታሪክ የሚሠሩበት ትልቅና
ወርቃማ አጋጣሚ በመሆኑ ኩራትም ክብርም
ይሰማኛል በግሌ፡፡
ሀትሪክ፡- …በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ
ማግኘት ሲገባት አላገኘችም ብለህ በቁጭት
የምታነሳት ሀገር አለች…. ?
በአምላክ፡- …እኔ ከውድድሩ በፊትም
ግምቴ አልጄሪያ ስለነበረች ከዚህ አንፃር
ዋንጫ ማግኘት ሲገባት አጥታለች ብዬ
በቁጭት የማነሣት ሀገር የለችም…፤…
ሻምፒዮን መሆን የሚገባው ትክክለኛ ብ/
ቡድን የአፍሪካ ዋንጫን ወስዷል፡፡የመጀመሪያ
ግምቴም ትክክል መሆኑን ዋንጫ በመውሰድ
አረጋግጠውልኛል፤ ግን እንደው ካነሣን
አይቀር በቁጭት ማንሣት ያለብን የግብፅን ብ/
ቡድን ነው፡፡ ብዙ ርቀት እስከ ዋንጫ ድረስ
መሄድ ሲገባት የቀረች ቡድን አለች ከተባለ
ግብፅን ልናነሳ እንችላለን፡፡ የግብፅ ብ/ቡድን
ጥሩ ብ/ቡድን ሆኖ እስከ ዋንጫ መሄድ
ሲገባው መንገድ ላይ መቅረቱ ቡደኑ ካለው
ጥንካሬና ከስብስቡ እንዲሁም የላቀ ስም
ከመያዙ አንፃር በአስቆጪነት ሊነሣ ይችላል፡፡
ሀትሪክ፡- …የአንተን የዘንድሮ የአፍሪካ
ዋንጫ ኮከብ ተጨዋች ጥራ ብልህ ማንን
ታስቀድማለህ…?
በአምላክ፡- …የአልጄሪያ ብ/ቡድን
አምበል የሆነው 9 ቁጥሩ ባግዳዳ ባውንጃህ
ለእኔ የውድድሩ ኮከብ ተጨዋች እሱ ነው…፤…
የመጫወት ክህሎቱ፣ድፍረቱ፣አልሸነፍ
ባይነቱ፣ ከጨዋታ ውጪ (ኦፋሲይት) አቋቋሙ
ለረዳት ዳኛ አስቸጋሪ መሆኑ፣ቡድኑን ለብቻው
ይዞ መውጣት የሚያስችል ትልቅ ስኪልን
(ችሎታን) ከምርጥ ተክለ ሰውነት ጋር ያለው
ተጨዋች ስለነበር በሁሉም መልኩ የእኔ ኮከብ
ተጨዋች እሱ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ብዙዎች ማዳጋስካርን
የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ክስተት
(ሰርፕራይዝ) ቡድን ብለው ይጠሯታል…
የአንተ ሰርፕራይዝ ቡድን ማን ነበር…?
በአምላክ፡- …የቤኒን ብ/ቡድን…፤…ለእኔ
የውድድሩ ሰርፕራይዝ ቡድን ቤኒኖች ናቸው፡
፡ ቤኒኖችን ከዚህ በፊት አንድ የማጣሪያ
ጨዋታ ላይ አይቻቸው ነበር፤ ያኔ ያየሁትና
አሁን ያየሁት በፍፁም አይገናኝም…፤…
የውድድሩ አስገራሚ ቡድን ለእኔ ቤኒኖች
ነበሩ፡፡
ሀትሪክ፡- …አሁን አንተ ሀገራችን ብቻ
ሣይሆን አህጉራችንም አለማችንም ካሏቸው
ምርጥ ዳኞች አንዱ ለመሆን በቅተሃል…፤…
በትክክል እኔን ይተካል ሀገሩንም ያስጠራል
የምትለው ዳኛ ማነው…?
በአምላክ፡- …ካሉን 7 ኢንተርናሽናል
ዳኞች ሁለትና ሶስት የሚሆኑ ኢንተርናሽናል
ዳኞችን በአፍሪካ መድረክ ይነግሳሉ ከፍ ብለው
ይታያሉ…፤…ከእኔ በላይ የተሻለ ብቃት
ያላቸው በአጭር ጊዜ የአፍሪካ የውድድር
መድረክን መቆጣጠር የሚችሉ ምርጥ ዳኞች
አሉን ጠብቅ፡፡
ሀትሪክ፡- …በአሁን ሰዓት ከበአምላክ
ውጪ ሌላ ዳኛ ስለመኖሩ ለማያውቁ በዚህ
ደረጃ የተማመንክባቸው ዳኞች እነማን ናቸው
በስም ጥቀስልኝ እስቲ…?
በአምላክ፡- …በነገራችን ላይ ካሉን ዳኞች
ብቃት ያለው በአምላክ ብቻ ነው በሚለው
አልስማማም…፤… ምናልባት በአምላክ ብቻ
ነው የተሻለው የሚባለው በእድሜና በልምድ
ከሆነ አንጣላም ልንስማማ እንችላለን…፤…
ግን እውነቱን ልንገርህ ከእኔ የተሻለ አቅም
ያላቸው ዳኞች አሉን፡፡ በቀጣይ መድረኩን
የሚቆጣጠሩ ሁለት ሶስት ምርጥ ዳኞች
አሉን…፤…የሚያስፈልገው እነዚህን ዳኞች
ማገዝ፣ ማበረታታት፣ መንከባከብ ብቻ
ነው…፡፡…በዘንድር የአፍሪካ ዋንጫ ሌሎች
ሀገሮች በሶስትና አራት ዳኞች ተወክለው
ነው የቀረቡት…፤…እኛም ይሄንን ነው
መፍጠር ያለብን፡፡ በሚቀጥለው የአፍሪካ
ዋንጫ ከብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ጋር በመሆን
የዳኞቻችንን ቁጥር ከፍ አድርገን ለማሳተፍ
መስራት ይኖርብናል፡፡
ሀትሪክ፡- በአምላክ ብዙዎችን ግር ያሰኘ
ወይም ያከራከረ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፤
ባለምጡቅ አዕምሮው፣ ሣይንቲስቱ፣ የስነ
ህዋ ተንታኝ የሚሉ የተለያዩ የአድናቆት ቅፅል
ስም ያለው የዘጠኝ አመቱ ሮቤል የአንተ ልጅ
ነው…?
በአምላክ፡- …አንተም ብዥታዎችን
ለማጥራት ይሄን ጥያቄ በማንሳትህ ደስተኛ
ነኝ፤ በሥጋ እኔ አባቱ ነኝ፤ እናቱም በሥጋ
እናቱ ናት፤ ከዚያ ውጪ ሮቤል በአምላክ
ማለት የመድሃኒአለም ስጦታ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-ከኮምፒዩተር፣ከማሽን በላይ
የሆነ አዕምሮ ባለቤት ነው…በማለት ብዙዎች
የአንድናቆትና የውዳሴ መዓት እያወረዱበት
ነው…፤…ይሄ ሁሉ የላቀ እውቀትን በዘጠኝ
አመት ከየት አመጣው…? ምስጢሩስ
ምንድነው…?…እናንተስ ምን የተለየ ድጋፍ
ታደርጉለታችሁ…?
በአምላክ፡- …እንዳልኩህ ነው…ሮቤል
የመድሃኒአለም ስጦታ ነው…፤… ለሮቤል
አዕምሮ ከእኛ ይልቅ የላይኛው ጌታ ያደረገው
ነው የሚበልጠው…።…እውነት ለመናገር እኛ
ምንም የተለየ ነገ\ር አላደረግንለትም…እንደ
አባትና እናት ፍላጎቱን እንጠብቃለን…፣…
በምንችለው መጠን እናሟላለን፣
እናበረታታለን፣.የሚፈልገውን የቴሌቪዥን
ፕሮግራም የውጪውን የመከታተል ፍላጎቱን
እንጠብቃለን፣ እናበረታተዋለን፡፡ ከዚህ
በዘለለ መጽሐፉ ቅዱስ በጣም ያነባል…፤…
ምን የተየለ ምስጢር አለው…?… የሚለውን
ራሱ ባለቤቱ መድሃኒአለም ብቻ ነው
የሚያውቀው…፤…ከዚህ በላይ ስለ እሱ
ማለት አልችልም፤የሁሉም ፀሎት አይለየን
ብቻ ነው የምለው፡፡
ሀትሪክ፡- …በአፍሪካ ዋንጫ
በአንድ ጨዋታ ያውም በወሳኝ
የጥሎ ማለፉ ፍልሚያ ሶስት ፍፁም
ቅጣት ምት (ፔናሊቲ) የሰጠህ ብቸኛ
ሰው ትመስለኛለህ…፤…በአንድ
ጨዋታ ሶስት ፔናሊቲ መስጠት
አይከብድም…?
በአምላክ፡- …በጣም
ይከብዳል…!…እንደዚህ አይነት
አጋጣሚ በዳኝነት ህይወቴ ገጥሞኝ
አያውቅም…፡፡ ግን ሶስት ፔናሊቲ
እንድሰጥ ያስገደደኝ የጨዋታው
ይዘት…የጨዋታው ክብደ የፈጠራቸው
ነገሮች ናቸው…፡፡…ግን እግዚአብሔር
ይመስገን VAR በመጨረሻ ላይ
በሰጠሁት ፔናሊቲ ላይ ስህተት
እንዳልፈፅም አግዞኛል…፤…በዚህ
እድለኛ ነበርኩ ማለት ይቻላል…፡፡
ሀትሪክ፡- …በካፍ ቻምፒዮንስ
ሊግ ጨዋታ ዊዳድ ካዛብላንካ እና
ሆራዩ ሲጫወቱ ግብ ጠባቂው
መጎዳቱን ተከትሎ ስቅስቅ ብለህ
ማልቀስህ የብዙዎች መነጋገሪያ
ከመሆን ባለፈ ምን ያህል አዛኝ ልብ
እንዳለህም ያሳየ ነው…፤…እንደዚህ
እንዲህ መቆጣጠር እስኪያቅትህና
እስከማልቀስ ስላደረሰህ አጋጣሚ
መለስ ብለህ አጫውተኝ እስቲ…?
በአምላክ፡- …ውይ እሱ
አጋጣሚ መቼም በቀላሉ ከውስጤ
የሚጠፋ አይደለም…፤…በህይወቴ
እንደዚህ ደንግጬ እንባዬ ድንገት
የፈሰሰበትን፣ያዘንኩበትን አጋጣሚ
አላስታውስም፡፡…ነገሩ እንዴት መሰለህ
የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ሆራያ
እና ዊዳድ ካዛብላንካ ነበር የሚጫወቱት…
ጨዋታው 4ለ0 እያለ አንድ ረዥም ኳስ
ከግራ ክንፍ በኩል ይላካል፤ አጥቂው ይሮጣል
ተከላካዩም እንደዚሁ ይሮጣል፡፡ ኳሱን ግብ
ከመሆን ለማዳን በፍጥነት የመጣው የ34
አመቱ ሴኔጋላዊው ግብ ጠባቂ ካህዲም ንዲዬ
ከራሳቸው ተጨዋች ጋር ይጋጫል…፤…
ኳሷንም የዊዳዱ አጥቂ ያገባዋል፡፡ በወቅቱ
የወደቁት ተጨዋቾች ጋ ስደርስ የሴኔጋል ብ/
ቡድንና የሆራያ ግብ ጠባቂ በጣም ተጎድቷል…
እግሩ ለሁለት ተከፍሏል…፤…ያየሁትን
ማመን አቃተኝ…. የሆነ በጣም ሆረር አይነት
ነገር ነው የተመለከትኩት፤ ሳላስበው ሌላ
ስሜት ውስጥ ገባሁ…ስሜቴን መቆጣጠር
አቃተኝ…ሳላስበው እንባዬን ለቀኩት፡፡ ዝም
ብለህ አስበህዋል ቡድንህ 4ለ0 እየተመራ 5ኛ
ጎል መግባቱ ላይቀር በዚህ ደረጃ መስዋዕትነት
ለመክፈል ስትጋደልና ያንን ተከትሎ ዘግናኝ
ጉዳት ሲደርስ…?…በቃ ይሄ ሁኔታ ነው
ስሜቴን እንዳልቆጣጠር ያደረገኝ…፡፡

ሀትሪክ፡- …ለሰው ልጆች ያለህን አዛኝነት
በዛ ቅፅበት ከገለፅክ በኋላ የነበረው ምላሽስ
ምን ይመስል ነበር…?

በአምላክ፡- …የብዙዎች መነጋገሪያ
እንደነበር አውቃለሁ…፤…ሁኔታው በጣም
የሚረብሽ ነው…፡፡ ከዚህ ቅፅበት በሃላየእኔና
የተጨዋቾቹም አዕምሮ ተሰረቀ…፤…
ሁለቱም ቡድኖች መጫወት አልቻሉም…፡፡
የቀረው አምስት ደቂቃ አካባቢ ቢሆንም አንድ
ደቂቃ ያህል ለማጫወት ሞክሬ ጨዋታውን
አቋረጥኩት፡ ከዚያ በኋላ ያደረኩት ነገር
ምንድነው…ለኢንተርናሽናል ፉትቦልስ አሶሲዬ
ሽን ቦርድ በዳኝነት ሕግ ላይ ለሚሠሩ የእግር
ኳስን ሰብዓዊነት ማሳየት አለብን…ጎሉም
ሣይድን የበረኛው እግር ለሁለት ተገምሶ
መፅደቅ የለበትም…ይሄን በማድረግ የእግር
ኳስን ሰብዓዊነት በእንደዚህ አይነት አጋጣሚ
ማሳየት ይገባል…ብዬ ለመፃፍ ተገድጄ ምላሽ
ያገኘሁበት አጋጣሚ ነበር…፡፡


ሀትሪክ፡- …በአምላክ ሁሌም ለሀትሪክ
ለምታሳየው ተባባሪነት ከልቤ እያመሰገንኩ…
ከዚህ በላይም ከፍ በል…ብዬህ ከመለየቴ
በፊት ቀረ የምትለው ካለ…?
በአምላክ፡- …እንግዲህ እድሉን ስለሰጠ
ኸኝ እያመሰገንኩ በምስጋና ቦታ ልወስድብህ
ነው…ለእስከዛሬው የዳኝነት ህይወቴ አሁን
የደረስኩበት ደረጃ እንድደርስ… ለዚህ
የአፍሪካ ዋንጫ መሳካት ከእኔ በስተጀርባ
የነበሩትን በሙሉ ማመስገን ይገባኛል…፤…
ምክንያቱ እጃቸው ስላለበት…፡፡…በዚህ በኩል
ቅድሚያውን የምሰጠው ለፈጠረኝና ለረዳኝ
አምላኬ ነው፡፡ በመቀጠል ፍቅርን በቂ ጊዜን
ነጥቄያቸው ግን የምትወክለው አገርን ነው
ብለው ከጎኔ በመሆን ድጋፋቸውን ለሰጡኝ
ቤተሰቦቼን፣የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና
የአዲስ አበባን እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ከልብ
አመሰግናለሁ፡፡ ዳኝነት በእኛ ሀገር የሙሉ
ጊዜ ሥራ አይደለም ከዚህ አንፃር “ልክ እንደ
አትሌቶች አንተም የሀገርህን ስም እያስጠራህ
በመሆኑ እኛም ከጎንህ ነን” በማለት አሁን
ለደረስኩበት ደረጃና ላስመዘገብኳቸው ስኬቶች
ቁልፉን ሚና የተጫወተው የምሰራበት መ/
ቤት አርማን ሐንሰን ሪሰርች ኢንስቲቲዩት
የሥራ ኃላፊዎችንና በአጠቃላይ የድርጅቱን
ሠራተኞች ለድጋፋቸው ምስጋና ባቀርብ
ያንስባቸው እንደሆነ እንጂ እንደማይበዛቸው
ስለማምን እግዚአብሔር ይስጥልኝ
ማለትን እወዳለሁ፡፡ በመቀጠል ስንጠነክር
የሚያበረታቱንን ስንሳሳት አንዱን ከሌላው ዝቅ
ለማድረግ እንዳልሆነ ተረድተው ለሚያርሙን
ክለቦች…በጣም ቅንና የእድገታችን ምክንያት
የሆኑት የሰፖርት ቤተሰቦች…ስንሳሳት
ስህተታችንን የሚጠቀሙን፣ስንበረታ ጉልበት
የሚሰጡንን ሚዲያዎች በሙሉ እንዲሁም
ለዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት የአፍሪካ ዳኞች
ከእኔ የሚበልጡበትን ሳስረዳቸው “ምንም
ችግር የለም” ብለው ሙያዊ ድጋፉ ለሰጡኝ
የካፒታል ሆቴል ባለቤትና አሰልጣኞች
ለውድድሩ በብቃት ስለአዘጋጁኝ…በመጨረሻም
ለዚህ እንድበቃ ላስተማሩኝ መምህሮቼ…
የጨዋታ ታዛቢዎች፣ኢንስትራክተሮችና
ዳኞች ላደረጋችሁልኝ ነገር በሙሉ አልብ
አመሰናለሁ፡፡ የሀትሪክ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል
ሁሌም ከጎኔ በመሆናችሁ እንዲሁ እናንተንም
አመሰግናለሁ ማለትን እወዳለሁ፡፡

ሶስቱ የትግራይ ክልል ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ዱባይ ላይ የቅድመ ዝግጅት ጊዜ ሊያሳልፋ ነው

ኢትዮ-ነጃሺ ቱር ኤንድ ትራቭል ከትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በተዘጋጀው ይህ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ሻምፒዮኒ መቐለ 70 እንደርታ፣ስሑል ሽረ ና ወልዋሎ ዓድግራት ዩኒቨርሲቲ ተሳታፊ ይሆናሉ።ከኦገስት 26- መስከረም 4 2019 ለ 9 ቀናት በሚቆየው የዝግጅት ጊዜ ሥስቱም ክለቦች በነጃሺ ካፕ ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ያልተለመደው ከሃገር ውጪ የቅድመ ውድድር ዝግጅት በነዚህ ክለቦች መጀመሩ ሊበረታታ ሚገባውና ሌሎች ክለቦችም ሊከተሉት ሚገባ ነው።

ሀትሪክ በነገው እትሟ የሚወዷት ጓጉተውም የሚያነቧት የዘወትር ማክሰኞ ሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣዎ ነገ በገበያ ላይ ትውላለች፤ ሀትሪክ በእትሟ ምን ምን ጉዳዮችን ይዛ ወጥታ ይሆን?


ሀትሪክ በነገው እትሟ
የሚወዷት ጓጉተውም የሚያነቧት የዘወትር ማክሰኞ ሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣዎ ነገ በገበያ ላይ ትውላለች፤ ሀትሪክ በእትሟ ምን ምን ጉዳዮችን ይዛ ወጥታ ይሆን?
በሀገር ውስጥ ዘገባዋ በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ባተረፈላት THE BIG INTERVIEW አምዷ የሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር እና ጋዜጠኛ የሆነው ይስሀቅ በላይ በአሁን ሰዓት በአልቢትርነት ሙያው የራሱንና የአገራችንን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ እያስጠራ ያለውን ስኬታማውን ኢንተርናሽናል አልቢትር በአምላክ ተሰማን መውጫና መግቢያ አሳጥቶት ያነጋገረውን ቃለ-ምልልስ የምታስነብቦት ሲሆን ሌሎችም መረጃዎችን ጋዜጣዎ ትሰጦታለች፡፡
ሀትሪክ ስፖርት ከበአምላክ ጋር በነበራት ቆይታ አልቢትሩ ለተጠየቀው ጥያቄ በጥቂቱ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷታል፡፡
“የህዝቡ የደስታ ስሜትና ያሳየኝ ድጋፍ የበለጠ እንድሰራ እንቅልፍ እንዳጣም አድርጎኛል የሚልና
“የሚቀጥለውን የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ በመምራት ደስታው የተነጠቀውን ህዝቤን መካስ እፈልጋለሁ፡፡ ያለው ይገኝበታል።
ሀትሪክ በባህር ማዶ ዘገባዋም ለእናንተ ከምታቀርብሎት ውስጥ ለባርሴሎና ፊርማውን ያኖረው አንቷ ግሬዝማን “ከሜሲ ጎን ተሰልፌ ለመጫወት እጅግ በጣም ጓጉቼያለሁኝ” ስላለበት ምላሽ ስለ አርሰናሉ ስፔናዊ አዲስ ፈራሚ ሴባልስ ለክለቡ ስለሚጨምርለት አቅምና ተጨዋቹ ወደ ቡድኑ በመምጣቱ ስለተሰማው ስሜት የማንቸስተር ሲቲው RAHEEM STERLING
“የአዲሱ አመት የሊጉ ፉክክር ከመቼም ጊዜ ይበልጥ ጠንካራ እንደሚሆን ስለመናገሩና የሊቨርፑሉ ግዙፉ ተከላካይ VIRGIL VAV DIJK የወርቅ ኳስ ተሸላሚ መሆን ይችላል ወይንስ አይችልም በሚል ዘገባ ላይ ነገ ሀትሪክን ያገኟታል፤ ሀትሪክ ሌሎችም ሊያነቡት የሚችሉ ዘገባዎች አሏት፤ ሀትሪክ አታምልጥዎት፡፡