Author: hatricksport team

Hatricksport team

ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የጥሎ ማለፍ ውድድርን አስመልክቶ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ ተሰጠ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የ2011 ዓ.ም የጥሎ ማለፍ ውድድር ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ኢትዮጵያ ቡና ከ ሐዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ጋር ለመጫወት ኘሮግራም መውጣቱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ሐምሌ 5 ቀን 2011 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ ይህንን ጨዋታ ማካሄድ እንደማይችል ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሳውቋል ፡፡ ፌዴሬሽኑም ይህንኑ መሠረት በማድረግ ለተጋጣሚው ሐዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በደብዳቤ ለቀጣዩ ጨዋታ ማለፋን ከገለፀ በኋላ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ በድጋሚ ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም ለፌዴሬሽኑ በፃፈው ደብዳቤ ቀደም ሲል ሐምሌ 5 ቀን 2011 ዓ.ም መሳተፍ እንደማይፈልግ የገለፀበትን ደብዳቤ በመሻር የጥሎ ማለፋን ውድድር ለማካሄድ ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ በመወያየት በመጀመሪያው ደብዳቤ የኢትዮጵያ ቡና ያቀረበውን ጥያቄ መሠረት በማድረግ ወስኖ ለተጋጣሚው ቡድን ያሳወቀ በመሆኑ ሐምሌ 8/2011 ዓ.ም የተፃፈውን የጥያቄ ደብዳቤ ያልተቀበለ መሆኑን ዛሬ ሐምሌ 9 ቀን 2011 ዓ.ም በውድድር ዳይሬክቶሬት በተፃፈው ደብዳቤ ለክለቡ አሳውቋል፡፡

Via- eff

በመቐለ ከተማ የ10 ኪ.ሜ ሩጫ ውድድር ተካሄደ

 

በመቐለ ከተማ በሁለቱም ፆታዎች የ10 ኪሎ ሜትር ውድደር ዛሬ ተካሄደ።

ውድድሩ ስፖርት ባህል ያደረገ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር ብሎም ክልሉንና አገር ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶች ለማፍራት ዓላማ ያደረገ እንደነበር ተገልጿል።

መነሻውንና መድረሻው ሮማናት አደባባይ ባደረገው  ውድድር ከ9ሺህ የሚበልጡ አትሌቶችና የከተማው ማህበረሰብ ተሳትፏል።

በሁለቱም ፆታ ከአንደኛ አስከ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው  ውድድራቸውን ላጠናቀቁ አትሌቶች የገንዘብና የዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷል።

በወንዶች በተደረገው ውድድር አንደኛ የወጣው ገብረጅወርግስ ተክላይ 60ሺህ ብር ፤ሁለተኛ የወጣው ምሩፅ ውበት 30ሺህ ብር፤ሶስተኛ ለወጣው ኃይለማርያም ኪሮስ 20ሺህ ብር ተሸልመዋል።

በተመሳሰይ በሴቶች ውድድሩን ያሸነፉት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ በመውጣት ያሸነፉት ፈትየን ተስፋይ ፣ ጎይቶም ገብረስላሴና አበራሽ ምናሰቦ ሽልማቱን ተቀብለዋል።

ለሶስተኛ ጊዜ በከተማው የተካሄደው ውድድር የተዘጋጀው አትሌት ገብረእግዚብሔር ገብረማርያምና ባለቤቱ ወርቅነሽ ኪዳነ ባቋቋሙት ናትና ስፖርት ኤቨንትስ በተባለ ተቋም ነበር።

ውድድሩን ያስጀመሩት የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት አረፈ የማህበረሰቡ ስጋት እየሆኑ የመጡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመፈወስ ዓይነተኛ መፍትሄ ስፖርት መሆኑ ማወቅና መተግበር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

Via – Ethiopia news Agency

“ከጅማ አባጅፋር የለቀኩት ገንዘብ ተቀብዬ ወይም ሙስና ሰርቼ አይደለም ይሄ ስም ማጥፋት ነው” “ድሮ ቀለበት ያደረገ ተጨዋች ሽማግሌ ነበር የሚባለው” አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና (ሰበታ ከተማ)�

THE BIG INTERVIEW WITH : KIFLE BOLTENA

 

በዮሴፍ ከፈለኝ

ሀትሪክ፡- ሰበታ ከተማን እንዴት
ተቀላቀልክ.. ውድድርስ ነበረው?

ክፍሌ፡-ሰበታን ለማሰልጠን በጣም እፈልግ
ነበር… ቤቴ እዚያው አካባቢ ነው ለመስራትም
ይመች ስለነበር ባገኝ አልጠላም ነበር፡፡ ነገር
ግን ክለቡን ለማሰልጠን ጥያቄ አላቀረብኩም
ስራ አስኪያጁ ታዬ ናኔቻ የ3 አሰልጣኞችን
ስም በዕጩነት አቀረበ.. ማቅረቡንም ደውሎ
ነገረኝ ለግምገማ አሉ የሚባሉ ደጋፊዎች
ተጠርተው ስፖርት ቢሮው ተሰበሰቡና በሙሉ
በአንድ ድምፅ መረጡኝ የሜዳ፣ የደጋፊና
የበጀት ችግር የለም የሚል ቅሬታ ነበረባቸው
የክለቡ አመራሮች ጠርተው አነጋገሩኝ ስለኔ
ጀርባ ተነግሮቸው ስለነበር መረጡኝ ይሄ
አመት ካልተሳካ በጀቱ ይቀነሳል ቡድኑ
በጨዋታው ህዝቡን አላስደሰተም ወይም
ውጤት የለም ብለው ተስፋ በቆረጡበት ጊዜ
ነው የገባውት፡፡ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ቡድኑን
ማስገባት ትችላለህ ብለው ሲጠይቁኝ አዎ
መቶ በመቶ ቡድኑን ወደ ሊጉ አሳድገዋለሁ
ብዬ ቃል ገብቼ ስራውን ጀመርኩ፡፡ በእርግጥ
ውጤት ቢጠይፋ ግማሽ አመት ላይ የስራ
ባልደረቦቼ እንደተሰናበቱ ሁሉ እንደምሰናበት
አውቅ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቃልህ
በምንም መንገድ ከታጠፈ ለመባረር ቅርብ
ነው አምላክ ረድቶኝ ኃላፊነቴን በውጤት
በማጀቤ ተደስቻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ክፍያ ላይ ሰበታ ከተማ ደከም
ብሏል የሚሉ ወገኖች አሉ… አልተቸገርክም?
ክፍሌ፡- በክፍያ ኤሌክትሪክ፣ ወልዲያ፣
አዲስ አበባ ከተማ፣ ኢትዮጵያ መድን ሀዲያ
ሆሳዕና ይበልጡናል
ወደ 7ኛ ደረጃ ላይ ነው
የምንገኘው… ባለፉት
አመታት ግን በክፍያ
ሰበታ ከላይ ነበር፡፡ አሁን
ስፈርም ትልቁ 44 ሺ
ብር የሚከፈላቸው 5
ተጨዋች ብቻ ናቸው፤
የሌሎቹን ቀንሰህ
አስፈርም ተብዬ ነው
ያስፈረምኩት፡፡ ብዙ
ተጨዋቾች በተሻለ
ክፍያ ቡድኑን ለቀው
ወጥተዋል፡፡ ለዝግጅት
አዳማ ስሄድ 12
ወጣቶችን ይዤ ነው…
አዳማ የነበረን የሙከራ
ጊዜ እንጂ የዝግጅት
ጊዜ አይመስልም ነበር
ሰበታ በነዚህ ልጆች
እንዴት ፕሪሚየር ሊግ
ለመግባት ያስባል?
ክፍሌ ከ3 ጨዋታ
በላይ አይዘልም
ይባረራል ይሉኝ ነበር፡
፡ ዝግጅት በደንብ
ሳንሰራ ወደ ሰበታ
ተመለስን የመጀመሪያ
የወዳጅነት ጨዋታ
ስናደርግ በአዳማ 5ለ0
ተሸነፍንና ብዙ ሰው
ሳቀብን፤ እኔ ግን 32
ተጨዋቾችን አይቼ
ተጠቀምኩበት ከዚያ
በኋላ በየጨዋታው
እያስተካከልን ተስፋ
ሰጪ እንቅስቃሴ
እያየሁ መጣሁ…
ከመጀመሪያው ጨዋታ
ጀምሮ ጥሩ ሆንን
ከቡና ቢ የተገኙ፣
በሌሎች ክለቦች
የተሰላፊነት እድል
ያጡ… ሌሎች ልምድ
ያላቸው ተጨዋቾችን
አካተን የፈጣሪ ፍቃድ
ታክሎበት ውጤታማ
ሆንን፡፡ ሊጉን ስንጀምር
ኮምቦልቻን 2ለ1
ረታን ከዚያ በኋላ
ው ጤ ታ ማ ነ ታ ች ን
ቀጠለ ተጨዋቾቼ የኔን
የአጨዋወት ፍልስፍና
ተቀብለው ጥሩ አቋም
አሳዩ… ማንኛውም
አሰልጣኝ የራሱ
ፍልስፍና አለው እኔም
ለፍልስፍናዬ በሰጠውት
ልምምድ ደስተኛ ነበሩ ራሣቸውን ለማሳየት
ሲታገሉ ቡድኑን ውጤታማ በማድረጋቸው
ሰበታ ሊያልፍ ችሏል፡፡ ፔፕ ጋርዲዮላ
የእንግሊዝን ኳስ አይቻልም ሲባል ቆየና
በሁለተኛና ሶስተኛ አመቱ በተከታታይ የሊጉን
ዋንጫ አነሳ፡፡ ኳስ ጊዜ ይወስዳል ሰበታ ላይ
ግን በ3 ወር አብሮነት ውጤታማ መሆን
ችለናል፡፡ በከፍተኛ ሊግ ቆይታችን ከባድ ጊዜ
አሳልፈናል የኛን ምድብ ስመለከት ጠንካራ
ፍልሚያ እንደሚጠብቀን ተረድቼ ከቡድኑ
አባላት ጋር ያደረኩት ጥረት ተሳክቶልንና
ዳገቱን ተወጥተን ለድል በቅተናል አንድ
መንፈስ አንድ ልብ ኖሮን ግጥሚያዎቹ
በድል ተወጥተን ሣንሸነፍ ወደ ፕሪሚየር
ሊጉ አድገናል፡፡ በኛ ሀገር ማናጀር አትሆንም
ሙሉ ኃላፊነት ለአሰልጣኝ አይሰጥም
ከኮሚቴ ውስጥ አንዱ ካኮረፈህ አበቃ… ይሄ
ክስተት ሳይኖር በትዕግስት በጋራ ሰርተን
ውጤታማ በመሆናችን ከንቲባ ጽ/ቤት፣
የክለቡ አመራሮች፣ ረዳቶቼና ተጨዋቾቼን
በአጠቃላይ ሁሉንም የቡድኑን አባላት
እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለው፡፡

ሀትሪክ፡- የዳኝነቱ ነገር ጫና ነበረው
ማለት ይቻላል?

ክፍሌ፡- የዳኝነት ችግር ነበር… በውጤት
ደረጃ ካየነው ያለፍነው ለፍተን በላባችን
ነው ይሄን አረጋግጥልሀለሁ፡፡ ከኛ በፊት
እገሌ የሚባል ክለብ 15 ሪጎሬ ነው ያገኘው
ይባል ነበር፤ ገና ድልድል ሲወጣ ፌዴሬሽኑ
የአዲስ አበባ ክለቦች ስለወረዱ ለአዲስ አበባ
ድጋፍ እናደርግ ብሏል ተብሎ ተነግሮን ነበር
ግን በተግባር አላየንም… አንደኛ ዙር ላይ
የነበረብን ጫና ከፍተኛ መሆኑ ግን እውነት
ነው፡፡ ከአንድ ክለብ ጋር ስንጫወት 2
ተጨዋች በቀይ ወጥቶብናል በ8 ተጨዋቾች
1ለ1 ተለያየን፤

ሀትሪክ፡- ቆይ ቆይ…አንተ የተቀጣህበት
ጊዜ ነበር… የውሳኔውን ተገቢነት አትቀበልም?
ክፍሌ፡- በርግጥ ሜዳ ገብቻለው ነገር ግን
የተፃፈው ሪፖርት ልክ አይደለም ያሳፍራል
ዳኛ ከቦ ሊደበድብ ሲል በፖሊስ ታጅቦ ወጣ
ተብሎ 3 ወር ተቀጣሁ… የክለቡ አመራሮችና
ተጨዋቾቼ ደጋፊው ግን ውሸት ስለነበር ከጎኔ
ቆሙ፡፡ ይግባኘ ጠየኩ አዎ ወይም አይ ሳይባል
1500 ብር ከፍዬም ምላሽ ሳላገኝ ቅጣቱን
ጨረስኩ፡፡ ይሄ ያሳፍራል… ክለቡ ይግባኙ
ሳይመለስ ቅጣቱን ስለጨረሰ ያስያዘው ገንዘብ
ይመለስ ብሎ ጠይቆ ያም አልተመለሰም…
እንዲህ አይነት ክፍተት ነበር ከዚያ ውጪ
ወልዲያ ላይ ስንጫወት የኛ በረኛ በ20 ደቂቃ
ውስጥ በቀይ ወጣ ግን በ10 ልጅ አሸንፈን
ተመለስን… ጫናውን ተቋቁመን ያገኘነው
ድል በመሆኑ ነው ድላችንን ልዩ የሚያደርገው
ለፌዴሬሽኑ ለኛ የሚያዳላ ዳኛም አንፈልግም
ግን ፍትሀዊ ውሳኔ የሚሰጥ ዳኛ ይመደብልን
ብለን ጠይቀናል ምላሸ ግን አላገኘንም…
በእርግጥ ለህሊናቸው የሚያጫውቱ ዳኞች
እንዳሉ አንክድም የመጨረሻው ጨዋታ
ከቡራዩ ጋር ስንጫወት ጥሩ ዳኛ ገጥሞናል
የፕሪሚየር ሊግ ዳኛ ተመድቦ 1ለ0 ረታን…
ደሴ ከተማ እኛ ሜዳ ላይ መጥቶ ጥሩ
ዳኛ በማግኘታችን ጠንካራውን ጨዋታ
1ለ0 አሸነፍን… ለገጣፎ ላይ ስንጫወት ጥሩ
ዳኛ በመመደቡ ሁለታችንም ክለቦች ደስተኞች
ነበርን… ጨዋታው ከፍተኛ ትኩረት
ተሰጥቶት ልዩ ኃይል ከሰው እኩል ተመድቦ
በተካሄደ ጨዋታ 1ለ1 ወጥተን በለገጣፎ
ሜዳ ላይ ማለፋችንን አረጋገጥን… ጨዋታው
ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው የሚያሳየው
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ
ጭምር ተገኝተው ተከተትለውታል፡፡
ሀትሪክ፡- በሰበታ ከተማ የአሰልጣኝነት
ቅጥር የተፈፀመው በታዋቂ ደጋፊዎች
ተመርጠህ ነው መሆኑን ገልፀሃል.. አሰልጣኝ
በደጋፊ መመረጡ ተገቢ ነው?

ክፍሌ፡- እንደዚህ አይነት ነገር
አይመረጥም… ነገር ግን ብዙ አሰልጣኝ ባለፉት
8 አመታት ተቀጥረው ሰርተው ውጤታማ
ሳይሆኑ ተሰናብተዋል.. ሰበታን ያልያዘ
አሰልጣኝ ቢቆጠር ትንሽ ነው.. አመራሮቹ
ሰልቸት ብሏቸዋል፡፡ ይህን ለማስወገድ ስራ
አስኪያጁ 3 ሰው በዕጩነት አቅርቧል…
ደጋፊውንም መረጃ ለመጠየቅ ተገደዋል፡
፡ አምናም 30 አሰልጣኝ ለቦታው ተወዳድሮ
በስዩም ከበደ በ1 ነጥብ ተበልጠሀል ተብዬ ነው
የቀረሁት፡፡ በግሌ ለቅጥር ውድድርም መኖሩን
አልደግፍም በየክለቡ የሰከነ ባለሙያ ቢኖር
ለክለቤ ውጤትና ለምንፈልገው አጨዋወት
ይሄ አሰልጣኝ ይሻላል ብሎ መርጦ ቢቀጥር
ነው የሚሻለው፤ አሁን ይሄ የለም፡፡ አሰልጣኙ
እድል ተሰጥቶት ለውጥ ከታየ ለአመታት
በቦታው ላይ እንዲቀመጥ የሚያደርግ ክለብና
አመራር በሀገር ደረጃ እንኳን የለም፡፡

ሀትሪክ፡- ከፕሪሚየር ሊጉ የዋንጫ
አሸናፊነት በላይ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር
ሊግ ማደግ ከባድ ነው የሚሉ አሉ…
ትስማማለህ?

ክፍሌ፡- እውነት ነው… ዳኛ ለመዳኘት
የሚቸገርበት ሊግ ነው፡፡ ገና ከሜዳ ውጪ
ስትሄድ አቻ ትመርጣለህ.. ዘግተህ 1ለ1
ወይ 0ለ0 ከሆንክ ትደሰታለህ… የአየር ላይ
ኳስ ይበዛዋል ከጨዋታ ውጭ ብትሆንም
ትለቀቃለህ…ሪጎሬ ሊሰጥብህ ይችላል አብዛኛው
ሜዳ አስቸጋሪ ነው የሚዲያ ትኩረትም
የለውም ፌዴሬሽኑ በካሜራ አያስቀረፅም
ይሄ ሁሉ መስተካከል አለበት ከዚህ ውጪ
በታዛቢዎች አላምንም ብዙ ታዛቢዎች ጥሩ
ቢሆኑም ለዳኛ በውሸት የሚያዳሉ ኮሚሽነሮች
አሉ አብረው ስለሚጓዙና የሙያ ባልደረባው
ስለሆነ አጥፍቶም ቢሆን እሱን ማስቀጣት
አይፈለጉም ፖለቲካው ያመጣው ችግርም
አለ… ስለዚህ ህዝብ ይፍረድ ሊጉ የቀጥታ
ስርጭት ይኑረው ሱፐር ሊጉ ላይ አንድም
ካሜራ የለም ካለም ባለሜዳው የሚያቀርበው
ነው ወደ ሊጉ ያለፉት ክለቦች በመርፌ ቀዳዳ
እንዳለፉ ቁጠረው፡፡

ሀትሪክ፡- ሰበታ ከተማ ለዳኞች ምንም
ገንዘብ አልከፈለም እያልክ ነው?

ክፍሌ፡- በፍፁም አላደረግንም… ብንከፍል
ኖሮ እኔ 3 ወር አልቀጣም ነበር፤ ብዙ ነገሮችን
ማድረግ ቀላል ይሆን ነበር… ነገር ግን በዚህ
ውስጥ ሰበታ ከተማ የለበትም ኮምቦልቻ ላይ
4ለ0 ስናሸንፍ ወልዲያን በሜዳው ስንረታ
ደጋፊዎቻቸው እያጨበጨቡ ነው ሆቴል
ድረስ የሸኙን ይሄ መሞገስ አለበት… እኛ በ22
ጨዋታ 1 ሪጎሬ ነው ያገኘነው ይሄ ክለባችን
ውጤትን ያገኘው በራሱ ላብ መሆኑን ያሳያል፡

ሀትሪክ፡- በዳኝነቱ ተበደልን የምትልበት
ጨዋታ የትኛው ነው?

ክፍሌ፡- በሜዳችን ፌዴራል ፖሊስን
ስናስተናግድ የመሀል ዳኛው ሶስት የፍፁም
ቅጣት ምት ከለከለን… ከተጨዋቾቼ ጋር
ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ይመላለሳል.. እልህ
ያስገባቸው ነበር ገና 3ኛ ጨዋታ እንደመሆኑ
ገና ከአሁኑ ለማን አድቫንቴጅ ለመስጠት
ነው? ብለን ጠይቀን ነበር በውሳኔውብንገረምም ሳንሸናነፍ 0ለ0 ተለያየን… ይሄን
መቼም አልረሳውም፡፡ ሁለተኛው ከገላን
ጋር ስንጨወት ሁለት ተጨዋቾች በቀይ
የወጡበትን ጊዜ አልረሳውም… አንደኛው
ጎል አስቆጥሮ ደስታውን ሲገልፅ ማሊያውን
አላወለቀም ነገር ግን ዳኛው ማሊያውን ወደ
ላይ አነሳ ብሎ ቢጫ ካርድ ሰጠው አምስት
ደቂቃ ሳይሞላ ፋውል ሰራህ ብሎ በ5 ደቂቃ
ውስጥ 2 ቢጫ አይቶ የወጣበትን አልረሳውም
በ8 ልጅ መከራችንን አየን… ሁለቱን ዳኞች
መቼም አንረሳቸውም፡፡

ሀትሪክ፡- በፕሪሚየር ሊግና በከፍተኛ
ሊግ መሀል የስም ለውጥ ነው ያለው እንጂ
የደረጃ ልዩነት የለም የሚሉ አሉ… እውነት
ነው?

ክፍሌ፡- በሊጉ ጠንካራ ተፋላሚ የሚሆኑና
ለውጤት የሚፋለሙ የተወሰኑ ክለቦች ናቸው
ሌሎቹ ላለመውረድና ከቻሉ መሀል ሰፋሪ
ለመሆን እንጂ ለውጤት አቅደው የሚመጡ
አይደሉም… በተለያየ ምክንያት ከሜዳ
ውጪ ማሸነፍ ይከብዳል የተጨዋቾች የደረጃ
ልዩነት የለም ምናልባት የአዕምሮ ዝግጅት
ወይም ጫና የመሸከም አቅም ቢለያይ እንጂ
ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ጅማ አባጅፋር ወደ ሊጉ
ባደገበት አመት ዋንጫ ወስዷል… ይሄ አንዱ
ማሣያ ነው ከባዱ ነገር የወረዱ ቡድኖች
ወደ ላይ ማደግ መቸገራቸው ነው ኤልፓ፣
ወልዲያ… አርባ ምንጭ…መድን ለማለፍ
ተቸግረዋል…. በእኔም እምነት በሁለቱ ሊጎች
ብዙም ለውጥ የለም፡፡

ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና
የከፍተኛ ሊግ ወይስ የፕሪሚየር ሊግ
አሰልጣኝ?

ክፍሌ፡- ራሴን የማየው የከፍተኛ ሊግ
አሰልጣኝ አድርጌ ነው የማየው… ብዙ
ኔትወርክ የለኝም ደጋፊ የለኝም ይሄ ደግሞ
ከፕሪሚየር ሊጉ አርቆኛል፡፡

ሀትሪክ፡-ኧረ እንዲያውም ኔትወርክ
እንዳለህ ነው የምሰማው?

ክፍሌ፡- (ሳቅ በሳቅ) የለኝም፤.. ውሸት
ነው ቢኖረኝማ ታችኛው ሊግ አልቀርም ነበር..
እንዲሳካልኝ ፈልገው የሚያግዙኝ ሰዎች አሉ
ወጣት ይዘህ ጥሩ ስለምትጫወት ደጋፊህ
ነን የሚሉኝ አሉ.. በማናቸውም ግን ተደግፌ
ክለብ ገብቼ አላውቅም በኔትወርክ የገባሁበት
ክለ የለም አለው ካሉ ይምጡ!

ሀትሪክ፡-የአንተ ስኬታማ ጊዜ መቼ ነው?
ክፍሌ፡- ስኬታማ ጊዜ የምለው በአየር
ኃይል የነበረኝ ጊዜ ነው ዋንጫ አላገኘሁም
ነገር ግን ርካታውን እፈለግ ነበር 25 ሰው
ለአሰልጣኝነት ተወዳደረ የክለቡ አመራር
የነበረው ኮ/ል ገ/ስላሴ የኔን ስም ሲያይ
ውድደሩ ሰረዘና አንተን ነው የምፈልገውና
አለኝ፡ በግሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ በመሆኑ
ስቴዲየም አይጠፋም… አትቅር ብትቀር
ወታደር ይዤ ነው የምመጣው ብሎ ቀልዶ
ቀጠሮ ሰጥቶኝ ሄድኩ… መግቢያ አዘጋጅቶ
ጠብቆ አስገባኝና ቁጭ ብለን አወራን ተግባባን
ሙሉ ኃላፊነቱ ተሰጠኝ… ጥሩ ቡድን ሰራሁ
የደብረዘይት አብዛኛው ነዋሪ የቢሾፍቱ ከነማ
ደጋፊ ነበር.. በኛ አጨዋወት ተማርከና የኛ
ደጋፊ ሆነ… 15 ኦራል መኪና ሙሉ ደጋፊ
መጥቶ ያየን ጊዜ ሁሉ ነበር… ቡድኑን
በነፃነት በምፈልገው መንገድ ሰርቼ ስላሣየሁ
በጣም ረክቻለው ይሄን ጊዜ ልረሳውም፡፡

ሀትሪክ፡- ለአሠልጣኝ ሀጎስ ደስታ ትልቅ
ፍቅር አለህ አሉኝ… እውነት ነው?

ክፍሌ፡- ጋሽ ሀጎስ ነፍሳቸውን ይማርና
ምርጥ አሰልጣኝና መካሪዬ ነበሩ… ቢሮ
ውስጥ ምንም ስለማትሰራ ስልጠና ውሰድ
የምትሰጠው ሀሳብ ጥሩ ነው በትምህርት
አዳብረው ብለው መከሩኝ የፕሮጀክት ስልጠና
ወስድኩ ወዲያውኑ የኤልፓን ሲ ቡድን
ሰጡኝ… አዲስ ተሰጥኦ ያለውን ተጨዋች
ማየት ጀመርኩ ኤልፓ ውስጥ ተጨዋቾችን
መዝገበህ ነው የምትመርጠው …እኔ ግን
ከዚያ ሃሳብ ወጣው.. እነ ዳንኤል የሻውን
ከአፈርሳ ሜዳ ነው ያገኘኋቸው… ብዙዎችን
ከተለያየ ቦታ ወስጄ ፈተንኳቸው በምርጫ ጊዜ
ወደ 3 ሺህ ታዳጊ ይመጣል.. እድሉ ደረጄ
ሲ ሞክሮ ወድቋል ፒያሳ ሲጫወት አይቼ
ግን አመጣሁት… አለማየሁ ዴልፒየሮ 5ኛ
ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ አስፓልት ላይ ሲጫወት
ነው ያየሁት፡፡ በሁለት እግሩ የሚጫወት
ተጨዋች ነበር… መልምዬ አጣርቼ ለአገር
የሚጠቅም አንድ ትውልድ አፍርቻለሁ..
ለብሔራዊ ቡድኑም መጥቀም ችለዋል፡
፡ ሰበታም በተመሳሳይ ነው የመለመልኩት..
ተሰጥኦ ያለውን መለየት ርካታ ያለው ጨዋታ
ማየት ያስደስተኛል… በአጠቃላይ በመብራት
ኃይል የነበረኝን ቆይታና የጋሽ ሀጎስ ውለታን
አልረሳውም፡፡

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ቡና ቆይታህ ትልቁ
ችግር ምን ነበር?

ክፍሌ፡- ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ከባዱ
ነገር እቅድ አለመኖሩ ነው፡፡ ሪያል ማድሪድ
ባርሴሎናን በገንዘብ ይበልጣል፡፡ ባርሳ
ይህን ለመብለጥ ምን ሰራ የሚለው ነው
ጥያቄው? በአንድ ዘመን የጨዋታ ፍልስፍና
ነው ጋርዲዮላ ከ10 በላይ ዋንጫ ያነሳው…
በወጣት አምኖ ሁለት ሶስት አመት እቅድ
ይዞ መስራት አልያም ገንዘብ አውጥቶ ብሎ
ኮከቦችን መግዛት… ኢትዮጵያ ቡናዎች
ከሁለቱ አንዱን መምረጥ አለባቸው…
በአንዱ ሃሣብ ለማመን የማመንታት
ችግር ነው ያለው፡፡ የደጋፊ መጮህ
የተለመደ ነው ውጤት ከጠፋ ይጮሃል
እቅድ ከያዝክ ተቃውሞን መቻል
አያቅትም… ኢትዮጵያ ቡናን 5
አመት ነው ያሰለጠንኩት…. ሆላንድ
ኮርስ እንድወስድ አድርጎኛል
ለማንም ያላደረገውን ነው ለእኔ
ያደረገው… ውጤት ሲጠፋ ግን
ተሰናበትኩ… እቅድህን ወስነህ
መጓዝ ይጠበቃል.. ይሄ ነው
ችግሩ…. ካሳዬ አሁን ሊመጣ
ነው ይባላል… ቢበላሽበትም
በትዕግስት ጊዜ ሰጥተው መጠበቅ
አለባቸው… ማንቸስተር ሲቲ
ባይታገሰው ጋርዲዮላ 2
ተከታታይ አመት የፕሪሚየር
ሊጉን ዋንጫ አያገኝም ነበር ይሄ
ትዕግስት ይጠበቅባቸዋል ባይ
ነኝ… አንዳንዴ እድለኛ ከተኮነ
ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ
ሊመጣ ይችላል፡፡ እግዚአብሔር
ረድቶኝ ነው በአጭር ጊዜ የተሳካልኝ፡፡
በእግር ኳስ ግን ትዕግስትና ጊዜ ወሳኝ
መሆኑን ክለቦቻችን ማመን አለባቸው፡፡

ሀትሪክ፡-በኤልፓ ተሰላፊነትህ ምርጡ
ጊዜህ መቼ ነበር?

ክፍሌ፡-ኤሊያስ ጁሃር፣ ጠንክር አስናቀ፣
ክፍሉ መብራቱ፣ እነ ሸዋንግዛው.. እነ አንጀሎ
በነበሩበት ቡድን ውስጥ ቋሚ ተሰላፊ ነበርኩ…
የኢትዮጵያ ሻምፒዮናና የአሸናፊዎች አሸናፊ
ዋንጫን በ1985 ወሰደናል… ሁለትዮሽ
ዋንጫ የወሰደው ይሄ ቡድን ለእኔ ምርጡ
ነበር… በነገራችን ላይ የኤልፓ ባህል ደስ
ይላል… አስቀድሞ ታዳጊውን ቡድን የያዘው
ቢረጋ ነበር ከዚያ እኔ ያስኩ…ቀጥሎ ኤልያስ
ጁሃር አሰልጥኗል… ክለቡን በሚያውቁ
የቀድሞ ተጨዋቾች መሰልጠኑ ነው ምርጥ
ተጨዋቾች እንዲፈሩ ያደረገው… የአሁኑ
የክለቡ ችግር ይሄን ባህል ባለማስቀጠሉ
የመጣ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ጥሩ ጎን ያኔ
በእኔ የሰለጠኑት አሁን አሰልጣኝ መሆናቸው
ነው፤ ዳንኤል የሻው፣ ሲሳይ.. ኃይሉ/ቻይና/
እነርሱ ለዚህ ምሳሌ ይሆናሉ፡፡

ሀትሪክ፡- አሁን ግን በታዳጊ ደረጃ
ለመወዳደር የሚፈልግም ወጣትኮ ጠፋ?

ክፍሌ፡- (ሳቅ) አንዴ እድሉ ደረጄ ሲናገር
ሰምቻለው… ከክፍሌ ጋር ለቢ ምርጫ ስንሄድ
ወደ 2 ሺህ ታዳጊ ይመዘገብ ነበር ሁሉም
ስለሚችሉ መምረጥ ይከብደናል… አሁን ግን
ታች ሄጄ ሳይ የመጡት 100 አይሞሉም
አንዱም ግን አይችልም አለ… ችግሩ ታዲያ
የሜዳ ችግር ይሁን ትውልዱ ወይም ተስፋ
መቁረጥ በዝቶ አሊያም ታች ያለው ስልጠና
አልገባኝም …ያኔኮ ትውልዱ ወደ ኳስ
ያዘነብላል ሜዳ እንደጉድ ነበር አሁን ግን ያ
ሜዳ የለም ይሄ ትልቅ ችግር ነው… ሌላው
ደግሞ ተጨዋቹ እስከ 13 አመቱ ድረስ በራሱ
ሊጫወት ይገባል፡፡ ከዚያ በኋላ ቢሰለጥን
ይሻላል ባይ ነኝ አለበለዚያ በአሰልጣኙ ፍላጎት
ይቀረፅና ያለውን ተሰጥኦ ያጣል ይሄ ነው
የሚመስለኝ… ለማን.ዩናይትዶቹ የፈርጊ
ቤቢስ ስኬት የቢ አሰልጣኙን ነው የማደንቀው
ጊግስና ቤካም አብረው ነው ያደጉት የተለያየ
ተሰጥኦ አላቸው ይሄን ጠብቆ ባላቸው ችሎታ
ማሰራቱ ነው ያሳደጋቸው… ጊግስን ድሪብል
ከምታደርግ እንደ ቤካም ረጅም ኳስ ተጫወት
ቢለው አይሆንም… ነገር ግን የሁለቱን
ችሎታ ቡድን ውስጥ መጠቀም ይችላል
ፈርጉሰን ያደረጉት ይሄንን ነው የቢ አሰልጣኙ
ያላቸውን አስቀጠለ እንጂ አላስተዋቸውም
በጣም የማደንቀውም ለዚህ ነው የታዳጊን
አቅም ለማየት የራሱ መነፅር ያለው አሰልጣኝ
ሊኖረን ይገባል፡፡

ሀትሪክ፡- ይህንን የሚያደርግ አሰልጣኝ
አለን ታዲያ?

ክፍሌ፡- (ሳቅ በሳቅ)
ሀትሪክ፡-በኛ ሀገር ደረጃ የራሱ ፍልስፍና
ያለው አሰልጣኝ አለን?

ክፍሌ፡- ስለማንም ማውራት አልሻም
(ሳቅ) ተው… ኳሱ የሚጥመው አንተም
የራስህን እኔም የራሴን
ከተጫወትኩ ነው ሳይንሱ
አንድ ነው አጨዋወቱ
ነው ልዩነት የሚፈጥረው አለበለዚያ ማንም ማሰልጠን
ይችላልኮ ብትወድቅ ብትነሣ በራስ አስተሳሰብ ነው መጓዝ ያለብህ.. ይሄ ካልሆነ ከባድ
ነው፡፡

ሀትሪክ፡-ጨዋታ አይቶ
በማንበብ ምርጥ የምትለው
አሰልጣኝ ማነው?

ክፍሌ፡- የ ኤ ል ፓ ው
ቢረጋ… ስዩም አባተ
ይመቹኛል፡፡ አሁን ደግሞ
በተወሰነ መልኩ ጥሩ ቡድን
እየሰራ ነው የሚባልልት
ምናልባት የማየት እድል ባላገኝም ውበቱ
አባተ ይመስለኛል… ስዩም አባተ ግን ልዩ
ነው ምክትል አሰልጣኝ ሆኜ ሰርቻለሁ
ይደፍራል.. ጎበዝ ነው… ከሁሉም በላይ ግን
ጋሽ ሀጎስ ደስታ ልዩ ናቸው… ታዳጊዎች
ሲጫወቱ ይመለከትና ሁሉንም ዝግጅት
ይዤ ነው የምሄደው ይላል… ዋናውን ቡድን
ተስፋውንና ታዳጊውን ቡድን ሁሉንም
ያያል አሁን ይሄን የሚያደርግ አሰልጣኝ
አለ? የለም.. ዝግጅት ላይ ጠንካራ ከሆኑ በቃ
ተሰላፊ ናቸው ለዚህ ነው ኤልፓ ቤት ከክለቡ
አልፈው ለሀገር የሚጠቅሙ ተጨዋቾች
የሚወጡት… ሌላው አሰልጣኞች ሰከን
ብለው አይሰሩም… ውጤት ተኮር ከሆንክ
ለህይወትህ ነው የምትሰራው ለህይወትህ
ከሰራህ ደግሞ ትክክለኛውን ስራ አትሰራም…
ላለመባረር ለእንጀራ ቤተሰቤ ምን ይበላል
ካልክ ደፍረህ ለመወሰን ትቸገራለህ፡፡ ብዙ
ክለብ የቆ 7 ወይም 8 ተጨዋቾች በአንድ
ክለብ ውስጥ ታያለህ ይሄ ውጤት ላይ
መተኮሩን ያሳያል አሰልጣኙ ታዲያ
ምን እየሰራ ነው እነዚህ ተጨዋቾችኮ
አሰልጣኞች ናቸው አካል ብቃትን
ማስተባበር ነው የአሠልጣኙ ስራ..?
አስተባባሪና አሰልጣኝኮ ይለያያል /
ሳቅ በሳቅ/ መልፋት ታዳጊ ላይ
ማመን ውድቀትም ቢሆን ለህሊህ
ደስታ ይፈጥራል፡፡ ውጪ ሀገር
የሚሰራበት ስልጠና አለ በተለይ
ለኛ ሀገር የሚጠቅመንን ማየት
የኛ ፋንታ ነው እኔም ኤልፓ
እንደነበርኩት አይደለሁም
አሁን.. ያኔ ለእርካታ ነበር
የምጫወተው አሁን ግን ማራኪ
አጨዋወት ከማሸነፍ ጋር የግድ
መሆኑ ገብቶኛል አሰልጣኞች
ወጣት ላይ ማመንና መድፈር
አለብን፡፡

ሀትሪክ፡- ውጤታማ ከነበርክበት
ከጅማ አባጅፋር አሰልጣኝነትህ ለምን
ወጣህ?

ክፍሌ፡- ስሜታዊ መሆኔ ነው…
ስራዬን ለማስከበር የሄድኩበት መንገድ
ልክ አልነበረም ለተጨዋቾች እረፍት
መስጠቴ ነው ያጋጨን… አላባ ላይ 1ኛ
መሆናችንን ስናረጋግጥ ለተጨዋቾቼ እረፍት
ሰጠው 1ኛ ዙር ካለቀ ማረፍ አለባቸው
ብዬ አምናለሁ፡፡ አላባ ላይ እረፍት ስሰጥ
ፕሬዚዳንቱ ሁሴን ደወለና አስተዳደሩ
ይጠብቅሃል ለምን እንዲህ አደረክ አለኝ
ከዚያ በፊትም ለተጨዋቾቼ ፍቃድ ሰጥቼ
ስለነበር ለምን ሰጠህ ብለው መተዳደሪያ
ደንብ አወጡልኝ ከፌዴሬሽኑ ደንብ ውጪ
አልቀበልም አልኳቸው፡፡ 1ኛ ዙር ካለቀ
በኋላ ደካማና ጠንካራ ጎናችንን ለመገምገም
ተቀመጥን… ግምገማው ላይ እያለ እንዲህ
አደረክ ብለው የማይሆን ነገር ሲዘረዝሩ
ተበሳጨሁ… ብድግ አልኩና በዚህ አይነት
ከዚህ በኋላ ብሰራ ውጤታማ አልሆንም
አልኳቸውና ለቀክኩ… በርግጥ በዚህ ተግባሬ
ተፀፅቻለው ይሄ ነው ምክንያቱ በቃ…

ሀትሪክ፡- እኔ የሰማሁት ከ3 ታዳጊዎች
ብር በመቀበልህ መሰናበትህን ነው….ውሸት
ነው?

ክፍሌ፡- በፍፁም… የተሳሳተ መረጃ
ነው… በወቅቱ የነበሩ ሰዎችኮ
አሁንም አሉ እነርሱን መጠየቅ
ይችላል… ከጅማ አባጅፋር
የለቀቅኩት ገንዘብ ተቀብዬ ወይም ሙስና
ሰርቼ አይደለም ይሄ ስም ማጥፋት
ነው፤ ወደፊት እውነቱ ይወጣል
አሰልጣኞች ጋር
ያለ ክፍተት ነው እርስ በርስ
ስ ለማ ን ከ ባ በ ር  ያ ወ ሩ ብ ኝ
አ ሰ ል ጣ ኞ ች አለ… ደስ የሚለኝ
የትም ክለብ ስሄድ ይችላል ነው
የ ም ባ ለ ው … የፊት ለፊት ሳይሆን ማስረጃ
የማይቀርብበት የ ማ ይ ታ ይ ነገር ያወራሉ ይሄ በሽታ
ይ መ ስ ለ ኛ ል ፡ ፡ አንዱ ዋና አሰልጣኝ
ሌላው ምክትል ለመሆን
ሰበታ ድረስ ሄደው አስወርተውብኛል ግን
አልተሳካም… ወደፊት እውነቱ ይወጣል፡፡

ሀትሪክ፡- መጠጥ
ታበዛለህ አሉኝ.. .እውነት
ነው?

ክፍሌ፡- (ሳቅ በሳቅ) ተጨዋች ሣለው
እኔና ኤሊያስ ጁሃር አብረን አንድ ክፍል
ነበር የምናድረው… ሁለታችንም ልንጠጣ
እንጠፋለን እኔና በለጠ ወዳጆ አብረን ነበር
የምናድረው ለሊት ትራስ ሰርተን ሄደን
አሰልጣኝ ወንድማገኝ ከባደ አውቆብናል…
ጠዋት ላይ በሩን ከፍተው ሲያዩ እኛ የለንም
ትራሱን ሲያዩ ስቀው ይወጡና ቁርስ ላይ
ተገናኘን… ደህና መስለን ስንገባ አሰልጣኙ
ወንድማገኝ የተቀበለኝ በጥፊ ነበር (ሣቅ)
አሁን ድረስ ያነሳዋል በዚህ አጋጣሚ ታሟል
ጤናው እንዲመለስ እመኛለሁ፡፡ ረጅም ጊዜ
አልተጫወትኩም ምክንያቱም መዝናናት አበዛ
ስለነበር ነው.. ቤተሰብንና ራስን ለመምራት
ጠጪ ከመሆን መታቀብ አለብን.. ከኔ ልትማሩ
ይገባል ማለት እፈልጋለው. ለነገሩ የአሁኑ
ጊዜ አብዛኞቹ ተጨዋቾች ትዳር ይዘዋል ይሄ
ጥሩ ነው፡፡ መቀጠል አለበት ሰበታ ከተማ
ውስጥ ቀለበት ያሰሩ 2 ተጨዋቾች አሉ በነርሱ
ደስተኛ ነኝ ድሮ ቀለበት ያደረገ ተጨዋች
ሽማግሌ ነበር የሚባለው ድሮኮ ሁለት ሶስት
የሴት ጓደኛ የነበራቸው ተጨዋቾች ነበሩ…
ይሄ አሁን የለም ለአላማ የሚኖር በዝቷል
በዚህ ቀጥሉ ለቀሪ የጨዋታ ህይወታችሁና
ለተስተካከለ ኑሮ መዝናናት ባያበዙ ጥሩ ነው
እላለው፡፡

ሀትሪክ፡- ከሰሞኑ የባለስልጣናትና የጦር
ሰዎች ግድያ መላው ህዝቡ አዝኗል.. ምን
ተሰማህ…?

ክፍሌ፡-ሰው ሲሞት የማያዝን የለም
ወንድም ወንድሙን ሲገድል ተረጋጋቶ
መስራት ይከብዳል የተለየ ሀገር የለንም
አንድ ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት፡
፡ በተፈጠረው ድርጊት ቅር ብሎኛል፡
፡ ትክክለኛ ምርጫ ተካሄዶ አሸናፊዎቹ
የሚመሯት ኢትዮጵያ ብትኖር ደስ
ይለኛል፤… ምናልባት በመነጋገር ማመን
አለብን ባይ ነኝ፡፡ ወደ ኋለኛው ዘመን
እየተመለስንኮ ነው አዕምሯችን አድጎ
ማየት እፈለጋለው ወንድም ወንድሙን
ገድሎ ምንም አያመጣም.. ወደ ድህነት
ኋላቀርነት እየሄድንኮ ነው ይሄ መታረም
አለበት ለሟቾች ቤተሰቦች፣ ጓደኞች፣
የቅርብ ሰዎችና ለመላው ህዝቡ መፅናናትን
እመኛለው፡፡

ሀትሪክ፡-የእግር ኳሱ ችግርስ አያሰጋም..
ይሄ ዘረኝነቱ ስጋት አይፈጥርም?
ክፍሌ፡- በጣም ስጋት አለው.. ህዝቡ
የሚወደው እግር ኳስም ሊጠፋ ነው…
የብሔር ስም ያላቸው ቡድኖች መቆም
አለባቸው የከተማ ስም ችግር የለም አለም
ላይም አለ.. ለምን ግን ወደ ብሔር ይሄዳል..?
ፊፋም ይሄን ይቃወማል..? አንዱ ሌላው ጋር
እየሄደ መደብደቡ ፊፋ ጋር አይደርስም ማለት
ይችላል? አንድ ቀን ልንታገድ እንደምንችል
እሰጋለው.. ፌዴሬሽኑ እገዳ ማድረግ ካለበት
መድፈር አለበት… የፊፋና የካፍ ህጎችን
መተግበር የግድ ነው… አለበለዚያ ቀጣዩ ጊዜ
ያሰጋናል፡፡

ሀትሪክ፡-ፎርማቱ ባለበት ይቀጥል ወይስ
ይቀየር?

ክፍሌ፡- ባለበት ይቀጥል ባይ ነኝ…
የችግሩ ምንጭ ፎርማቱ ነው ብዬ አላምንም
ከዚህ ይልቅ ህጎችን ማጥበቅ ነው የሚሻለው…
የፎርማቱ ለውጥ መፍትሄ ያመጣል ብዬ
አላስብም ስፖንሰር ፈልጎ ሁሉም ጨዋታ
በቀጥታ ቢሰራጭ ህዝቡ አይቶ ቢፈርድ
ለውጥ ይኖራል ብዬ አስባለሁ… እግር
ኳስኮ ከዘርና ከፖለቲካ የፀዳ ነው ባያበላሹት
እመርጣለሁ፡፡ ሌላው የፖለቲካ ሰዎች ብቻ
ቢሮ አካባቢ ባይበዙ… አይሁኑ ማለት
አይቻልም መንግሥት ብር ሰጥቶ አይቆጣጠሩ
ማለት አልችልም ነገር ግን የሙያ ሰዎች
በደንብ ቢካተቱ የኳሱ ችግር ሊቀንስ ይችላል
ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡-ጨረስኩ.. የምታመሰግነው ሰው
ካለ?

ክፍሌ፡- የምስጋና ቅድሚያውን
ለአምላኬ እሰጣለው ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ
እግዚአብሔር ይመስገን ብዙ ፈተናዎችን
አልፌ ለዚህ እንደደርስ አድርጎኛል.. ከርሱ
በመቀጠል ውዷ ባለቤቴን ትዕግስት…………..
አመሰግናለው፡፡ ኳስ መጫወት ካቆምኩም
በኋላ የነበረብኝን ደካማ ጎን ችላ ታግሳ
እያበረታታችኝ በትዕግስቷ በምክሯ ደግፋ
ለውጣኛለች፡፡ ስራ አቁሜ ከርሷ የተነሣ ምንም
አይነት ክፍተት አልተፈጠረም እግዚአብሔር
የሰጠኝ እርሷን ነው ረጅም እድሜ
እመኝላታለው ልጆቼን አሳድጌ በህይወት
ኖሬ የተገኘሁት ከእግዚአብሔር ቀጥሎ በርሷ
ነው አመሰግናታለው፡፡ ትዳር ከመሰረትን 20
አመታት ሞልቶናል ቀሪ ዘመናችንን የደስታና
የስኬት እንዲሆን እመኛለው ከዚያ በተረፈ
አዲሱ ከንቲባ፣ ቢሮ ውስጥ ያሉት የክለቡ
ኃላፊዎች፣ ጀግኖቹ ተጨዋቾቼ፣ ረዳቶቼ፣
ጫና ፈጥረው ለድል ያበቁን ደጋፊዎቻችን፣
ቤተሰቦቼን ስኬት እንዲገጥመኝ የተመኙልኝን
ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ሶስትዮሽ የዋንጫ ፍልሚያ አጓጊ ሆኗል

ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዋንጫ
ፍልሚያ በ3 የክልል ክለቦች መርሃ ግብር
መሆኑ አጓጊ ሆኗል፡፡

መሪው ፋሲል ከተማ አዳማ ላይ ከአዳማ ከተማ
ጋር 1ለ1 ተለያይቶ ሁለት ወሳኝ ነጥቦችን
ቢጥልም በግብ ክፍያ የሊጉን መሪነት አሁንም
ይዟል፡፡ በአዳማው ፍልሚያ ሙጂብ ቃሲም
ለፋሲል ከተማ ቡልቻ ሹራ ለአዳማ ከተማ
ባስቆጠሯቸው ግቦች በ53 ነጥብና 29 ግብ
ሊጉን ሲመራ መቐለ ላይ ደቡብ ፖሊስን 4ለ0
የረታው መቐለ 70 እንደርታ በእኩል 53
ነጥቦችና 19 ግቦች ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አቻ
ወጥቶ ያጣውን 2 ነጥብ ዳግም አግኝቶ ፉክክሩ
ላይ ነፍስ ዘርቶበታል፡፡ ለገ/መድህን ኃይሌ
ቡድን ማውሊ ሳውሊ 2 ግብ ሲያስቆጥር
ቀሪዎቹን አማኑኤል ገ/ሚካኤልና ያሬድ
ብርሃኑ አስቆጥረዋል፡፡ ድሬደዋን በሀብታሙ
ገዛኸኝ ግብ 1ለ0 የረታው ሲዳማ ቡና በ52
ነጥብ ፋሲል ከነማና መቐለ 70 እንደርታ ላይ
ደረስኩ እያለ ጫናውን በማሳደር ላይ ይገኛል፡
፡በቀሪው መርሃ ግብሮች ፋሲል ከነማ ከቅ/ጊዮርጊስ በሜዳው ከስሁል ሽረ ጋር ከሜዳው
ውጪ ይጫወታል፡፡ መቐለ 70 እንደርታ
በበኩሉ ከመከላከያ ጋር ከሜዳው ውጪ
ከድሬደዋ ጋር በሜዳው ሲጫወት ሲዳማ ቡና
ከሜዳው ውጪ ስሁል ሽረን በሜዳው ደግሞ
ወልዋሎ አዲግራትን ይገጥማል፡፡


29ኛ ሳምንት መርሀ ግብር
ረቡዕ ሰኔ 26 ቀን 2011
04:00 ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ስሑል ሽረ
09:00 ባህር ዳር ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር
09:00 ወላይታ ድቻ ከ አዳማ ከተማ
09:00 ደቡብ ፖሊስ ከ ኢትዮጵያ ቡና
09:00 ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ
09:00 ደደቢት ከ ሲዳማ ቡና
09:00 ፋሲል ከነማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ
09:00 መከላከያ ከ መቐለ 70 እንደርታ


 

“መከላከያን የምንፋለምበት ጨዋታ የዋንጫ ነው” “በዋንጫ ፉክክሩ የሚያሰጋን ሲዳማ ቡና ነው” ሄኖክ ኢሳያስ /መቐለ 70 እንደርታ/�

በመሸሻ ወልዴ

መቐለ 70 እንደርታ በፕሪበመቐለ ሊጉ
የ28ኛው ሳምንት ጨዋታው በወራጅ ቀጠና
ላይ የሚገኘውን ደቡብ ፖሊስን 4ለ0 በማሸነፍ
ከሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ ጋር ያለውን የሁለት
ነጥብ ልዩነት በማስተካከል አሁን ላይ በእኩል
ነጥብ ሊጉን በጋራ እየመሩት ሲገኝ ፋሲል
ከነማ የቅድሚያ ስፍራ ላይ ሊቀመጥ የቻለው
በግብ ክፍያ በመብለጥ ብቻ ነው፡፡
የመቐለ 70 እንደርታ እግር ኳስ ክለብ
የፕሪምየር ሊጉን በግብ ክፍያ እየመራ
ከሚገኘው ፋሲል ከነማ ጋር ዋንጫውን
ለማንሳት እየተፎካከረ ባለበት የአሁን ሰዓት
ላይ የቡድኑ የግራ መስመር የአማካይ
ስፍራ ተጨዋች ሄኖክ ኢሳያስ ቡድናቸው
የዘንድሮውን የሊግ ዋንጫ የሚያነሱበት
ዕድል እንደተመቻቸላቸውም ይናገራል፡፡
የመቐለ 70 እንደርታው ሄኖክ በዚህ
ዙሪያም አስተያየቱን ሲሰጥ “መቐለ የፕሪምየር
ሊጉን ዋንጫ የማንሳት እድሉ የሚወሰነው
ከመከላከያ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ነው፤
ግጥሚያውን ማሸነፍ ይኖርበታል፤ ስለዚህም
ከእነሱ ጋር የሚኖረን ጨዋታ የዋንጫ ነው
ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል፤ የመቐለ 70
እንደርታው ሄኖክ ጋር በክለባቸው የፕሪምየር
ሊግ የውድድር ዙሪያና በራሱም የኳስ
ህይወት ቆይታው ላይ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ
/G.BOYS/ አናግሮት ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ጅማሬህ ምን
ይመስላል?

ሄኖክ፡- የእግር ኳስን መጫወት
የጀመርኩት ተወልጄ ባደግኩበት የሐረር
ከተማ ጀጎል አካባቢ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በቤተሰብ ውስጥ የእግር
ኳስን የምትጫወተው አንተ ብቻ ነህ? ስንት
ወንድምና አህት አለ?

ሄኖክ፡- በቤተሰባችን ከሚገኙት መካከል
የአሁን ሰዓት ላይ የእግር ኳስን የምጫወተው
እኔ ብቻ ነኝ፤ አክስቴ ቀድሞ እንደነገረችኝ
ከሆነ ደግሞ አሁን ላይ በህይወት የሌለው
ወላጅ አባቴም ኳስን ይጫወት ነበር፤ እኛ
ቤት ውስጥ አሁን ያሉኝ እህቶች ሶስት ሲሆኑ
አንድ ወንድምም አለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን ስትጫወት
ቤተሰብ አካባቢ የነበረው አመለካከት እንዴት
ነበር?

ሄኖክ፡- ቤተሰቦቼ ትምህርት ላይ
እንዳተኩር የሚፈልጉ ቢሆንም ያኔ ኳስ
መጫወቱም ላይ አይጫኑኝም ነበር፤
ስለዚህም የምወደውን እና የማፈቅረውን ኳስ
በመጫወት እና ጠንክሬም በመስራት ነው
የዛሬው ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻልኩት፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ ክለብ ተጨዋችነት እንዴት
ገባህ?

ሄኖክ፡- የእግር ኳስን ስጫወት ወደ ክለብ
ደረጃ የገባሁት ባህርዳር ላይ በተካሄደው
ውድድር ሐረርን ወክዬ በፕሮጀክት ደረጃ
ስጫወት ነው፤ ያኔም ደደቢቶች አይተውኝ
ነው ለወጣት ቡድናቸው ሊያስፈርሙኝ
የቻሉት፡፡

ሀትሪክ፡- ደደቢት የመጀመሪያው ክለብህ
ነው፤ ቆይታህን እንዴት ትገልፀዋለህ?

ሄኖክ፡- ደደቢት ከወጣት ቡድኑ
አንስቶ እስከዋናው ድረስ የተጫወትኩበት
እና ለዛሬም ጥሩ የኳስ ህይወቴ መንገዱን
የከፈተልኝ ቡድኔ ነው፤ በዚህ ቡድን ውስጥም
ለስምንት ዓመታት ያህልም ተጫውቻለው፤
በዚህ ቡድን ቆይታዬም የፕሪምየር ሊጉን
ዋንጫ ያነሳው ስለሆንኩም በዚህ በጣም
ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
ዋንጫን ከደደቢት ክለብ ቆይታህ በኋላም
ዓምናም ከጅማ አባጅፋር ጋር ለማንሳት
ችለሃል…

ሄኖክ፡- አዎን፤ ይህን የሊግ ዋንጫ
ከአንዴም ሁለት ጊዜ በወጣትነት እድሜ ላይ
ማግኘት መቻል መታደል ነውና የእኔ ደስታ
ልዩ ሊሆንልኝ ችሏል፤ ዘንድሮ ደግሞ ፈጣሪ
አሳክቶት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ዋንጫ
ማግኘት ከቻልኩ የዋንጫ ቁጥሬ ሀትሪክ
ይሆንና ደስታዬ የበለጠ የሚጨምርልኝም
ይሆናል፡፡

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን ልጅ ሆነህ
መጫወት ስትጀምር ተምሳሌትህ ማን ነበር?

ሄኖክ፡- የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ
ነበርኩና ሪያን ጊግስ ነበር ሞዴሌ፤ ለእሱ
ችሎታ ልዩ አድናቆት ነው ያለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታን
በፕሪምየር ሊጉ የውድድር ተሳትፎ እንዴት
አገኘኸው? ጠንካራ እና ደካማ ጎናችሁ ምን
ነበር?

ሄኖክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
ላይ ያለንን የዘንድሮ ተሳትፎአችንን በሁለት
መልኩ ነው የምገልፀው፤ ውድድሩ ሲጀመር
እኔ የቡድኑ ተጨዋች ያልነበርኩ ቢሆንም
በጥሩ የውጤታማነት ጉዞ ላይ ነበር ይሄድ
የነበረው፤ በሁለተኛው ዙር ላይ ክለቡን
ስቀላቀል ደግሞ ከሜዳ ውጪ ባደረግናቸው
ጨዋታዎች ተደጋጋሚ የውጤት ማጣት
ስላጋጠመን እና በሜዳችንም ነጥብ የጣልንበት
ሁኔታ ስለነበር በዚህ የሊጉን ውድድር በሰፊ
ነጥብ ልንመራ የምንችልበትን ውጤት
አሳጥቶን በፋሲል ከነማ እንዲደረስብን
አድርጓል፤ አሁን ላይ ደግሞ በድጋሚ ወደ
ውጤታማነት ልንመለስ ችለናል፡፡
የመቐለ 70 እንደርታ ጠንካራው ጎን
አንድነታችን እና ህብረታችን ነው፤ ከዛ
ውጪም አሰልጣኛችን ገብረ መድህን ኃይሌ
የሚሰጠንን ጥሩ እና ወጣ ያለ ስልጠናን
በሜዳ ላይ ተግባራዊ ማድረግ መቻላችን
ነው፤ ክፍተት ጎናችን ደግሞ የሜዳ ውጪ
ግጥሚያዎቻችንን አለማሸነፍ መቻላችን ነው፡

ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታ፣ ፋሲል
ከነማ እና ሲዳማ ቡና የፕሪምየር ሊጉን
ዋንጫ ለማንሳት ተፋጠዋል፤ በውድድሩ
መጨረሻ ማን ባለድል ይሆናል? ለእናንተስ
ከሁለቱ ስጋት የሚሆንባችሁ ክለብ ማን
ነው?

ሄኖክ፡- የዘንድሮውን የፕሪምየር
ሊጉን ዋንጫ የምናነሳውማ እኛ ነን፤
ይህም ድል ከመከላከያ ጋር በምናደርገው
ጨዋታ ይወሰናል፤ ለዋንጫው ለእኛ ስጋት
የሚሆንብንም ክለብ ሲዳማ ቡና ነው፡፡

ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታ ደቡብ
ፖሊስን ያሸነፈበት ጨዋታ የፋሲል ከነማን
አቻ መውጣት ተከትሎ በነጥብ እንዲጋራ
አድርጎታል፤ ግጥሚያው ምን መልክ ነበረው?

ሄኖክ፡- ደቡብ ፖሊስን በሰፊ የግብ
ልዩነት ያሸነፍንበት ጨዋታ ለእኛ ጣፋጭ
የሆነልን ድል ነው፤ ጨዋታውን ለመርታት
የአሰልጣኛችንን ምክር በሚገባ መስማት
መቻላችን ጠቅሞናል፤ ደቡብ ፖሊስ
ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን ነው፤ ያን
ስለምናውቅም አሰልጣኛችን ለእነሱ ጊዜ
መስጠት እንደሌለብን እና ጎልም ቶሎ
ማስቆጠር እንዳለብንም ስለነገረን ያንን ጎል
ማስቆጠር ከ16ኛው ደቂቃ አንስቶ ተግባራዊ
ስላደረግን እና እነሱም ጎል ሲቆጠርባቸው
በእንቅስቃሴ እንዲወርዱ ስላደረግን በዚህ ባለ
ድል ልንሆን ችለናል፡፡

ሀትሪክ፡- በህይወት ዘመንህ በጣም የተደ
ሰትክበት እና የተከፋክበት አጋጣሚ የቱ ነው?

ሄኖክ፡- በጣም የተደሰትኩት የፕሪምየር
ሊጉን ዋንጫ ዓምና ከጅማ አባጅፋር ክለብ
ጋር ስናገኝ ነው፤ የተከፋሁትና ያዘንኩት
ደግሞ ወላጅ እናት እና አባቴን በሞት ያጣው
ጊዜ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የመቐለ 70 እንደርታን
አሰልጣኝ እንደዚሁም ደግሞ ደጋፊዎቻችሁን
በምን መልኩ ነው የምትገልፃቸው?

ሄኖክ፡- የመቐለ 70 እንደርታው
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን ከወቅኩበት
ጊዜ ጀምሮ ለእሱ የማሰልጠን ችሎታ ከፍተኛ
ክብር እና አድናቆትም ነው ያለኝ፤ በደደቢት
ክለብ የተጨዋችነት ዘመኔ እኔን ከወጣት
ቡድኑ ችሎታዬን አይቶ ያሳደገኝ እሱ ነው፤
ወደ ጅማ አባቡናም ባመራሁበት ጊዜ ወደ
ክለቡ ያመጣኝ እሱ ነው፤ አሁንም ከወላይታ
ድቻ ወደ መቐለ 70 እንድራታ በሁለተኛው
ዙር ቡድኑን እንድጠቅም በድጋሚ ጠርቶኝ
በክለቡ ጥሩ ጊዜን እያሳለፍኩ ስለሆነ ይሄ
ያስደሰተኛል፡፡
የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎችን
በተመለከተ እነሱ እስከ 60 እና 70 ሺህ
ደጋፊዎች በመሆን የሚሰጡን ድጋፍ ልዩ
ነው፤ ለውጤታማነታችንም ማማር የእነሱ
ከፍተኛ አስተዋፅኦም አለበትና ሊመሰገኑ
ይገባል፡፡

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነት
የወደፊት ምኞትህ?

ሄኖክ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን
በመመረጥ ሀገሬን ማገልገል እፈልጋለው፤
ይሄን እድል ከዚህ በፊት ዕድሜያቸው
ከ23 ዓመት በታች ለሆነው የባሬቶ ቡድን
ውስጥ ተመርጬ ተጫውቼ ነበርና ሀገርን
ማገልገል የሚሰጠው እርካታ ከፍ ያለ ስለሆነ
በድጋሚ መመረጥን እፈልጋለው፤ ከዛ
ውጪም በፕሮፌሽናል ተጨዋችነትም ከሀገር
በመውጣት የመጫወት ፍላጎቴ ከፍተኛ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…..?

ሄኖክ፡- የእግር ኳስ ተጨዋችነት
ህይወቴ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ የረዱኝን
ማመስገን እፈልጋለው፤ መጀመሪያ ለፈጣሪዬ
ነው ምስጋናዬን የማቀርበው በመቀጠል
ለቤተሰቦቼ ማለትም ላሳደገችኝ አያቴ፣
ለአክስቴ፤ ለአክስቴ ባል እንደዚሁም እኔን
ከታዳጊነት እድሜ አንስቶ ላሰለጠኑኝ ነፍሱን
ፈጣሪ ይማረው ለፋሲል ተወልደ ለዳንኤል
ፀሐዬ ለገብረመድህን ኃይሌ እና ብዙ ነገር
ላደረገችልኝ ለታናሽ እህቴ ዮርዲ ከፍተኛ
ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለው፡፡

ሀትሪክ ስፖርት በማክሰኞ እትሟ ተወዳጅ ጋዜጣዎ ሀትሪክ ስፖርት እነዚህን ዘገባዎች በማክሰኞ እትም ይዛ ወጥታለች።

ሀትሪክ ስፖርት በማክሰኞ እትሟ
ተወዳጅ ጋዜጣዎ ሀትሪክ ስፖርት እነዚህን ዘገባዎች በማክሰኞ እትም ይዛ ወጥታለች።
ሀትሪክ በሀገር ውስጥ ዘገባዋ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ባተረፈላት THE BIG INTERVIEW አምዷ ሰበታ ከተማን ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሳለፈው አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና በስልጠና ህይወቱ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዬች ላይ ከጋዜጣው ጥያቄዎች ቀርቦለት ምላሽ ሰጥቷል።
ሀትሪክ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን አስመልክቶም የመቀለ 70 እንደርታው ሄኖክ ኢሳያስ በራሱ በሊጉና በክለቡ ዙሪያ ይናገራል።
ሀትሪክ የባህር ማዶ ዘገባዋም ላይ የአፍሪካ ዋንጫን አስመልክቶና በአውሮፓ የተጨዋቾች ዝውውር ዙሪያ መረጃን ይዛሎት ቀርባለች።
ሀትሪክ አታምልጦት ያንብቧት።

ሀትሪክ በነገው እትም ሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ በነገው እለት በገበያ ላይ ስትውል የሚከተሉትን ጉዳዮች ይዛ በመውጣት ለንባብ ትበቃለች፡፡

ሀትሪክ በነገው እትም
ሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ በነገው እለት በገበያ ላይ ስትውል የሚከተሉትን ጉዳዮች ይዛ በመውጣት ለንባብ ትበቃለች፡፡ ሀትሪክ በሀገር ውስጥ ከፍተኛ ተወዳጅነት ባተረፈላት THE BIG INTERVIEW አምዷ “መቐለ 70 እንደርታ የክቡር ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ወኪል አይደለም፤
በርሳቸው አሳቦ እኛን መሳደብና መደብደብም ተገቢ አይደለም…”
ሉን የሚከፋን ተዋጊዎች ስላልሆንን ነው፤ የፖለቲካ
ሰዎች አይደለንም በዚህ አትጥሩን እኛ የስፖርት ሰዎች ነን”
“የመቐለ ህዝብ የራሱን ክለብ እስኪያገኝ ድረስ የቡና ደጋፊ ነበር…” በሚል የክለቡ እግር ኳስ ስራ አስኪያዥ ከሀትሪክ ጋዜጣ የቀረበላቸውን ድፍረት የተሞላበት ጥያቄ እሳኛውም በድፍረት የመለሱ ሲሆን ከዛ ውጪምይቀጥላል”
በአስቸኳይ የተጠራው የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ
በፕሬዝዳንቱ ኢሳያስ ጅራ ትዕዛዝ አዘል ንግግር ስለመጠናቀቁ እና የተቋረጠው ሊግ ሊጀመር ስለመሆኑ ታስነብቦታለች፡፡
ሀትሪክ በባህር ማዶ ዘገባዋም ክሪስ ስሞሊንግ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ኦልድትራፎርድ ላይ የሚያደረጉት ጨዋታ እየናፈቀው ስለመሆኑ የሪያል ማድሪዱ አዲሱ ፈራሚ ስለሆነው ሄዲን አዛርድን ሌሎችም ዘገባ አላት፤ የነገዋ ሀትሪክ አታምልጦት ከዛ ውጪም ሌሎች ያልተሰሙ ዘገባዎችን ሀትሪክ ነገ ማለዳ ይዛ እጅዎ ትገባለች፡፡
የሀትሪክን ትኩስ የሆኑ መረጃዎቿን ከጋዜጣዋ በተጨማሪ በርካታ ተከታታዮች ባሏት hatricksport.com ድረ-ገፃችን ላይም ያገኛሉ። ይጎብኙን፡፡
የሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ የነገው የፊት ለፊት ገፅ ይህንን ይመስላል፡፡

አፍሪካ | ካፍ ለግብፁ አፍሪካ ዋንጫ ከኢትዮጵያ ሁለት ዳኞችን መመረጡ በይፋዊ ገፁ አስታወቀ

 

ከሳምንታት በኃላ በሚጀመረው የ2019 አፍሪካ ዋንጫ ከኢትዮጵያ ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ እና ረዳት ዳኛ ሳሙኤል ተመሰገን ውድድሩን እንደሚመሩ የመጨረሻውን የዳኞች ዝርዝር ይፋ በማድረግ አስታውቋል።

 

የአፍሪካን አህጉር በዋናነት እሚመራው ካፍ ፣ በዋና ዳኝነት 26 ዳኞች እንዲሁም በረዳት ዳኘነት 30 ዳኞች በግብፅ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ትልቁን ወድድር እንደሚመሩ ተገልጿል።

ለህትመት ሰኞ ዕለት ማተሚያ ቤት የገባችው ሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ እያለች በበዓሉ ምክንያት የእዚህ ሳምንት እትሟን በነገው ዕለት በገበያ ላይ ታውላለች፡፡

ለህትመት ሰኞ ዕለት ማተሚያ ቤት የገባችው ሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ እያለች በበዓሉ ምክንያት የእዚህ ሳምንት እትሟን በነገው ዕለት በገበያ ላይ
ታውላለች፡፡
ሀትሪክ ስፖርት ለገበያ ነገ ስትበቃም ምን ምን ጉዳዮችን ይዛ ወጥታ ይሆን? በሀገር ውስጥ ዘገባዋ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድርን አስመልክቶ ሊጉን ከሚመራው የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን ተጨዋቾች መካከል ስለክለባቸው ውጤታማነት እና ሌሎችን ጉዳዮች በማንሳት ጠንካራ ተጨዋቻቸውን ሽመክት ጉግሳን በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አናግረነው ምላሽን ሰጥቷል፤ ሀትሪክ ከዛ ውጪ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እሁድ ዕለት መካሄድ ስለነበረበት እና ሳይካሄድ ስለቀረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የኢትዮጵያ ቡናና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታና ግጥሚያው አዳማ ላይ በዝግ ስታድየም ይካሄዳል ስለመባሉና ቡና ስለሰጠው መልስ እንደዚሁም ደግሞ እየተባባሰ ስለመጣው የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት ዙሪያ ዘገባ አላት፡፡
ሀትሪክ ሌላው ከፍተኛ ተወዳጅነትን ባተረፈላት THE BIG INTERVIEW አምዷ የሲዳማ ቡናውን አሰልጣኝ ዘርኃይ ሙሉን በተጨዋችነት ዘመኑ ስለነበረው የስፖርት ህይወት፣ ስለስልጠና ዘመኑ፣ በአሁን ሰዓት ስላለው ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግሮች እንዲሁም ሌሎችም ጥያቄዎች ቀርቦለት ለጋዜጣው ምላሹን ሰጥቶበታል፡፡
ሀትሪክ ስፖርት በባህር ማዶ የነገ ዘገባዋም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታን አስመልክቶ ስለ ባለ ድሉ ሊቨርፑል እና ስለ ቡድኑ ተጨዋች ሞ.ሳላ እንደዚሁም ደግሞ ቼልሲ በድል ስላጠናቀቀው እና የሀዛርድ ምሽት ስለተባለበት የአውሮፓ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ሀትሪክ በጥሩ ዘገባዋ ታስነብቦታለች፡፡
የነገዋ ሀትሪክ አታምልጦት ከዛ ውጪም ሌሎች ያልተሰሙ ዘገባዎችን ሀትሪክ ነገ ማለዳ ይዛ እጅዎ ትገባለች፡፡
የሀትሪክን ትኩስ የሆኑ መረጃዎቿን ከጋዜጣዋ በተጨማሪ በርካታ ተከታታዮች ባሏት hatricksport.com ድረ-ገፃችን ላይም ያገኛሉ። ይጎብኙን፡፡
የሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ የነገው የፊት ለፊት ገፅ ይህንን ይመስላል፡፡
መልካም ንባብ